ባለፉት አመታት የዞኑን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ፖሊስ የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ ነው – የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር

ባለፉት አመታት የዞኑን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ፖሊስ የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ ነው – የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ባለፉት አመታት የዞኑን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ፖሊስ የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ ነው ሲሉ የቤንች ሸኮ ዞን አስተዳደር ገለፀ።

የቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ መምሪያ የ2015 ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና በግዳጅ አፈጻጸም የተሻለ ስራ ለሰሩ አካላት የዕውቅናና ሽልማት መርሀ ግብር በሚዛን አማን እየተካሄደ ይገኛል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ እንደተናገሩት በዞኑ ባለፉት አመታት የተለያዩ ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ ፀረ ሰላም ሀይሎች የፈጠሩት የፀጥታ ችግር በርካታ ዜጎች ለሞት የንብረት ውድመት ማስከተሉን ገልጸዋል፡፡

የዞኑ ፖሊስ ሠራዊት በየአካባቢው የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ከመከላከል ባለፈ የዞኑ ሠላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ፖሊስ የከፈለው መስዕዋትነት ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዞኑ ፖሊስ በከተማው የሚፈፀሙ የስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ከመከላከል ባለፈ በተለያዩ ጊዜያት የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ ከአካል ጉዳት እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ታሪክ የሚዘክረው ሰራ ሰርተዋል ብለዋል።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ዶክተር ካሳ በበኩላቸው የዞኑ ፖሊስ ወንጀሎችን አስቀድሞ ከመከላከል ባለፈ ወንጀል ተፈፅሞ ሲገኝም በተገቢው መልኩ ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

በበጀት አመቱ የህዝብንና የሀገርን ሠላም የሚነሱ የተለያዩ ትልልቅ የወንጀል ድርጊቶችን ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት መከላከል መቻሉን ተናግረዋል።

በተለይ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና 632 የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል።

የዞኑ ፖሊስ በ3ወረዳዎች በነበረው የፀጥታ ችግሮች ጫካ ገብተው የነበሩ 14 ፀረ ሠላም ሀይሎችን ከመደምሰስ ባለፈ ሌሎቹ በህግ ተጠያቂ እንዲኑ በማድረግ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በዞኑ ባለፉት ጊዜያት በግዳጅ አፈጻጸም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 138 የፖሊስ አካላት የዕውቅናና ሽልማት መርሐ ግብር ይሰጣል ተብሏል።

በመድረኩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችን ጨምሮ የዞንና የወረዳ አስተዳዳሪዎችና እንዲሁም ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን