በጌዴኦ ዞን ሲሰጥ የነበረው ክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና ተጠናቀቀ
ሀዋሳ፡ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጌዴኦ ዞን በሚገኙ 8 ወረዳዎች 5 ከተማ አስተዳደሮች ለ2 ቀናት ሲሰጥ የቆየው ክልል አቀፍ ፈተና መጠናቀቁን የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ ተናግረዋል፡፡
በዞኑ 13ሺህ 655 ተማሪዎች ለፈተና መቀመጣቸውንም ተጠቁሟል።
በ3 አከባቢዎች ላይ የሀሰት መልስ በማመላለስ ውዥንብር ሲነዙ የነበሩ ግለሰቦችን በህግ እንዲጠየቁ ከማድረግ ባለፈ፥ ፈተናው በሰላም መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ዘማች ቀጣይ በዞን ደረጃ ለሚሰጠው የ6ኛ ክፍል ፈተና ዝግጅት መጠናቀቁንም አክለዋል።
በዞኑ የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከሚሰጥባቸው ወረዳዎች አንዱ የቡሌ ወረዳ 733 ተማሪዎችን ማስፈተኑን የጠቀሱት የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ያሲን፥ ተማሪዎች ፈተናውን በራሳቸው አቅም እንዲሠሩና ኩረጃን ለማስቀረት ሰፊ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
በወረዳው ፈተናው በሰላም መጠናቀቁን የጠቆሙት አቶ ከድር ከቀጣይ ሐሙስ ጀምሮ ለሚሰጠው የ6ኛ ክፍል ፈተና ለ856 ተፈታኞች ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ታምራት አለማየሁና ፋሲካ ወልደሰንበት በቡሌ ወረዳ ዳሮ ማዕከል የ8ኛ ክፍል ፈተና ጨርሰው ሲወጡ ያገኘናቸው የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። ወረዳው ያዘጋጀላቸው ሞዴል ፈተና ለማጠቃለያ ፈተናው በደንብ እንዳዘጋጃቸው ተናገረው በሰላም በማጠናቀቃቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ከሣሁን – ከፍስሐገነት ጣቢያችን
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ