‎በቡና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች የውሃን ሀብት ከብክለት በመጠበቅ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጌዴኦ ዞን ግብርና መምሪያ አሳሰበ

‎ይህ የተገለፀው የዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና በ2018 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡

‎በዞኑ የንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትን ለመቅረፍ የሚከናወኑ ተግባራትን በመደገፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ላበረከቱት አስተዋጽኦ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ታጠቅ ዶሪ (ዕጩ ዶ/ር) አመስግነዋል፡፡

‎ምክትል አስተዳዳሪው አክለውም አሁን ያለንበት ወቅት የቡና ምርት የሚሰበሰብበት በመሆኑ በታጠበ ቡና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የውሃ ሀብትን ከብክለት በመጠበቅ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

‎በውይይት መድረኩ የጌዴኦ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪና የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ተመስገን ጥላሁን፤ የማዕድን አማራጮችን በጥናት ለይቶ ወደ ኢኮኖሚ በመቀየር ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባል ብለዋል፡፡

‎በዘርፉ በህገወጥ መንገድ በመሰማራት ለጥቅማቸው ሲሉ የህዝብንና የመንግስትን ሀብት የሚያባክኑ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ ህብረተሰቡ ለህግ አስከባሪዎች ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን እንዲወጣ ኢንጂነር ተመስገን አሳስበዋል፡፡

‎የጌዴኦ ዞን 48 የሚፈሱ ወንዞችና በርካታ ገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ የተፈጥሮ ፀጋ የተቸረው እንደሆነ የዞኑ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊ ዳዊት ጀቦ (ዶ/ር) በመናገር፤ በዚህም አርሶአደሩ ከዝናብ ጠባቂነት በመውጣትና የመስኖ አማራጮችን በመጠቀም እንዲያመርት በበጀት ዓመቱ በትኩረት እንደሚሠሩ ጠቁመዋል፡፡

‎በ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም የተሻለ ውጤት እዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሴክተር መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት እውቅናና የሽልማት ፕሮግራም በማጠቃለያው ተካሂዷል፡፡

‎ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን