ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት የቅድመ አንደኛ ላይ ትኩረት ማድረግ ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ: ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ቅድመ አንደኛ ላይ ትኩረት በማድረግ ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።
ሁለተኛው የትምህርት ጉባኤ “የትምህርት ጥራት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በወራቤ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተካሄደው ሁለተኛው የትምህርት ጉባኤ ላይ በቀረበው የውይይት ሰነድ ዙሪያ የማጠቃለያ አቅጣጫ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው፥ ለአጠቃላይ የትምህርት ጥራት መሠረት በሆነው የቅድመ አንደኛ ላይ ትኩረት ማድረግና ሁሉም አካል በዚህ ዙሪያ ሊረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትምህርትን ጥራት ለማሻሻልና ውጤታማ ለመሆን የተለያዩ የትምህርት ግብዓት ማሟላት እንደሚገባ የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የመንግስት፣ የባለሀብቶችን፣ የማህበረሰቡንና የግለሰብን አቅም መጠቀም እንደሚገባ ገልፀዋል።
በተለይ የመጽሐፍ ህትመት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ክልሉ የራሱን ማተሚያ ቤት ለማቋቋም መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
የመምህራን አቅም ማሣደግ እንደሚገባ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ተከታታይ ስልጠና መስጠት ተገቢ መሆኑን አሳስበዋል። በተለይ በተማሪዎች አያያዝ፣ በማስተማር ስነ-ዘዴ፣ በፈተና አወጣጥ (Table of specification)፣ እንግሊዝኛ ቀቋንቋ ማሻሻል ላይ ተከታታይ ስልጠና ሊሰጥ አንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
ከዚህ በተጓዳኝ በየደረጃው የሚገኝ አመራር ትኩረትና ክትትል ሊያደርግ አንደሚገባ ገልጸው፥ የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እየተሻሻለ መሄዱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ አስቴር እሸቴ በበኩላቸው፥ መንግሥት በትምህርት ጥራት ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን ለማረም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ከ 86 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የበርካታ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም በትምህርት ዘርፉ አይነተኛ ለዉጥ ማስመዝገብ መጀመሩን ጠቅሰዉ፥ የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበር የትምህርት ዘርፉን ዉጤታማነት በአጠረ ጊዜ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን መደገፍ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፥ ባለፉት ዓመታት የ2017 ት/ት ዘመንን ጨምሮ የትምህርት ብክነት በተለይም መጠነ-ማቋረጥ የሰለጠነና ምርታማ ዜጋ ለመፍጠር በምናደርገው ጥረት አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን አመላክተዋል።
በክልሉ እየተስተዋለ ላለው የት/ት ብክነት መንስኤዎች በጥናት የተለዩ በመሆኑ በተቀመጠው ምክረ-ሀሳብ መሠረት በተለይም የት/ት ብክነት ለመቀነስ ሁሉ-አቀፍ ጥረት በጋራ ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ መሠራታዊ ችግሮችን በተለመደው አሰራር ብቻ መፍታት እንደማይቻል ገልፀው፥ ትምህርት ቢሮ ኢንሼቲቮችን ቀርጾ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመው፥ በ2017 ትምህርት ዘመን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ኢንሼቲቭ በመቅረጽ ክልሉ ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሆሳዕና ት/ት ኮሌጅ በመተባበር ተግራዊ እየተደረገ መሆን አክለዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ዘላለም ተስፋዬ
More Stories
በጎፋ ዞን የደምባ ጎፋ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ተካሄደ
የሰንደቅ አላማ ቀን በዓል የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ አጠናክረን የምናስቀጥልበት ነው ሲሉ የቀቤና ልዩ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ተናገሩ
የሀገር ሉዓላዊ ክብር መገለጫ ለሆነዉ ሰንደቅ ዓላማ ተገቢዉን ክብር መስጠት እንደሚገባ የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ