የሀገር ሉዓላዊ ክብር መገለጫ ለሆነዉ ሰንደቅ ዓላማ ተገቢዉን ክብር መስጠት እንደሚገባ የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ

የሀገር ሉዓላዊ ክብር መገለጫ ለሆነዉ ሰንደቅ ዓላማ ተገቢዉን ክብር መስጠት እንደሚገባ የይርጋጨፌ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ
‎
‎በዛሬዉ ዕለት 18ኛዉ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከብሯል።
‎
‎በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ናዝሬት ዘኪዎስ እንደገለፁት፤ 18ኛዉ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የዘመናት ቁጭት ሆኖ የቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ማግስት የሚከበር መሆኑ ከሌሎች ጊዜያት ለየት ያደርገዋል።
‎
‎የወረዳው ነዋሪዎችም ሀገራችን ለጀመረችዉ ሁለንተናዊ ዕድገት እያበረከቱ ያሉትን ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸዉ ዋና አፈ ጉባኤዋ አሳስበዋል።
‎
‎የሰንደቅ ዓላማ ቀለማት የኢትዮጰያዊያን ጀግንነት መስዕዋትነት እንዲሁም የልማት አርበኝነት ማሳያ ናቸው ያሉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ቡኔ፤ ለትናንሽ አጀንዳዎች ጆሮ ባለመስጠት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሻገር ይገባል ብለዋል።
‎
‎የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና ነጻነት በቀደምት አባቶች ደምና አጥንት ላይ የቆመ ነው ያሉት አቶ ዳዊት ደህም፤ ትውልድ የታሪካዊ ሃገሩን ክብር የመጠበቅ አደራ አለበት ብለዋል፡፡
‎
‎የሀገራችን ሉዓላዊነት መገለጫ የሆነዉን የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ስናከብር ጀግኖች አባቶቻችን ላቆዩት ሀገርና ሰንደቅ ዓላማ ተገቢዉን ክብር በመስጠት ሊሆን እንደሚገባም አስተዳዳሪው አስገንዝበዋል።
‎
‎የሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል በፖሊስ ሰልፍ ትርዕይት፣ በሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ-ሥርዓት፣ መሪ ቃልና መልዕክቶችን በማስተጋባት እንዲሁም በሌሎች ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በልዩ ድምቀት ተከብሯል።
‎
‎በመርሃ ግብሩ ላይ የወረዳ አመራሮች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የፀጥታ አስከባሪዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
‎
‎ዘጋቢ: ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን