ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ሀገር መለያ፣ የሉዓላዊነትና የነፃነት ዓርማ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ገለፀ

ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ሀገር መለያ፣ የሉዓላዊነትና የነፃነት ዓርማ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ገለፀ

‎18ኛው የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን ”ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያ ታላቅ ከፍታ ዘመን ብስራት፤ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉአዊነታችንና ለኢትዮጵያ ህዳሴ” በሚል መሪ ቃል በአርባ ምንጭ ከተማ ተከብሯል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢተው እንደገለጹት፤ ሰንደቅ ዓላማ ለአንድ ሀገር መለያ ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነትና የነፃነት ዓርማ ነው።

‎ሰንደቅ ዓላማ የህዝባችን አንድነትና አብሮነት ምልክት፣ ጀግኖች ለክብሯ የተዋደቁላት፣ ለጥቁር ህዝቦች የነፃነትና የአይበገሬነት ምልክት ለሆነች ታላቅና ታሪካዊ ሀገር የተወከለችበት ዓርማ ነው።

‎ሰንደቅ ዓላማ ሀገራዊ አንድነትና አብሮነት ማጠናከሪያ በመሆኑ የሀገር ልማትንና ብልጽግናን የሚያስቀጥል እንዲሁም የሀገሪቱን ብሎም የክልሉን ህዝብ ሰላምና አንድነት ማስቀጠያ መሆኑንም አስረድተዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኦዲት መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ አበባየሁ ኤርምያስ፤ የዘንድሮው ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተጠናቀቀ ማግስት መከበሩ የዘንድሮውን ሰንደቅ ዓላማ ቀን ልዩ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

‎አቶ አበባየሁ አክለውም፤ የትናንት ፈተናን፣ አንድነት በመፍጠር በድል እንደተሻገርን ሁሉ የቀጣዩንም ለመሻገር አንድነትን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

‎የስንደቅ ዓላማን ምንነትንና ክብር ከማስረጽ አኳያ ሁሉም ባለድርሻ አካል የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

‎አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል ሳጂን ሰራዊት ኡቴ እና ረዳት ኢንስፔክተር ኤፍሬም መስፎ፤ሰንደቅ ዓላማ ለኢትዮጵያ ከፍታና ሉዓላዊነት የተከፈለ የመስዋዕትነት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል።

‎መርሀ ግብሩ ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል እና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም ተቋጭቷል።

‎ዘጋቢ፡ አስናቀ ካንኮ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን