ለሀገራዊ አንድነት፣ አብሮነትና የህብረብሔራዊ መገለጫ የሆነውን ሠንደቅ ዓላማን ማክበር ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደሚጠበቅ ተገለጸ

ብሔራዊ የሠንደቅ ዓላማ ቀን “ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል መሪ ቃል በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል።

ዕለቱን አስመልክቶ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሸካ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ዮሐንስ ካሳሁን እንደገለፁት፤ ሠንደቅ ዓላማ የሀገር አንድነት መገለጫ የህብረ ብሔራዊ አንድነት ኩራት ነው።

ለመላው የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ምልክት የሆነውን ሠንደቅ ዓላማ ክብሩን አስጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይጠበቃል ብለዋል።

“ሠንደቅ ዓላማችን ለኢትዮጵያ ታላቅ የከፍታ ዘመን ብሥራት፣ ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ሕዳሴ” በሚል የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሰለ ከበደ፤ ሠንደቅ ዓላማ የሀገራዊ አንድነትና የነፃነት መገለጫ ታላቅ የብሔራዊ ኩራት አርማ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሠንደቅ ዓላማ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት የሚከበር ታላቅ ሀገራዊ በዓል መሆኑን ያነሱት የበዓሉ ተሳታፊዎች፤ ለሠንደቅ ዓላማ ክብር በአንድነት መቆም ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

ዕለቱ ሠንደቅ ዓላማ በመስቀልና በሠንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ መሐላ በመፈፀም በድምቀት ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ የክልሉ ብዝሃ ማዕከል ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች፣ የሸካ ዞን አመራሮች፣ የመንግሥት ሰራተኞችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ: አስቻለው አየለ – ከማሻ ጣቢያችን