የቡና ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ ጥራቱን በማስጠበቅ ረገድ ተገቢ መረጃ መያዝና የባለሙያ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

የቡና ምርት እና ምርታማነት በማሳደግ ጥራቱን በማስጠበቅ ረገድ ተገቢ መረጃ መያዝና የባለሙያ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቡና ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ ጥራቱን በማስጠበቅ ረገድ ተገቢ መረጃ መያዝና የባለሙያ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ አዘጋጅነት በአዉሮፓ ህብረት ድጋፍ ከደን ጭፍጨፋ ነፃ ምርት አቅርቦት ደንብ እና በቡና ማሳ ልየታ መረጃ አሰባሰብ ዙሪያ ለቤንች ሸኮ ዞን እና ለምዕራብ ኦሞ ዞን የግብርና ባለሞያዎች ስልጠና ተሰጥቷል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል ለቡና ምርት ስነምህዳር ምቹ በመሆኑ በክልሉ የሚገኙ አብዛኛው ዞኖች እና ወረዳዎች በቡና አብቃይነት የሚታወቁ መሆናቸው ተመላክቷል።

በክልሉ 598ሺ ሄክታር ማሳ በቡና የተሸፈነ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል የምክትል ርእሰ መስተዳደር አማካሪ እና የግብርና ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ዬሐንስ መላኩ እንደገለጹት፥ የቡና ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ በሄክታር የሚገኘው ምርት ከአምስት ኩንታል ወደ አስር ኩንታል በሄክታር በአማካይ ለማሳደግ የቡና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተቀርጾ ወደተግባር መገባቱን ጠቁመዋል።

ክልሉ በሀገሪቱ ካሉ ክልሎች ቡናን ወደማእከላዊ ገበያ ከማቅረብ አንጻር ከኦሮሚያ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብ በተለይም ከደን ጋር ተቆራኝቶ የሚኖር እንደመሆኑ መጠን ደን ባለበት አከባቢ ሁሉ ቡና በመኖሩ፥ የቡና ምርት የተፈጥሮ ይዘቱን ጠብቆ እንዲመረትና በአለም አቀፍ ገበያ ተፈላጊ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።

ከቡና ገዢዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የአውሮፖ ህብረት ከደን ጭፍጨፋ ነጻ የሆነ የቡና ምርት ብቻ ነው የምንገዛው ብሎ ያወጣውን መስፈርት ለማሟላት እና መረጃውን በተገቢው አደራጅቶ ለመያዝ በክልሉ ቡና አብቃይ በሆኑ ወረዳዎች ለሚገኙ ለ1ሺህ 137 የግብርና ባለሙያ ሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል። በዚህም በዘንድሮ አመት 400 ሺ ሄክታር መሬት የቡና በመረጃ ለመያዝ ታቅዷልም ብለዋል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ሻይ ባለስልጣን የቡና ሻይ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ታዬ በበኩላቸው ስልጠናው የአውሮፖ ህብረት ከደን ጭፍጨፋ ንክኪ ውጪ ቡና ለመቀበል ባወጣው መስፈርት መሰረት የወጡ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ለባለሙያ የአቅም ግንባታ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ቡና ገዢ የአውሮፓ ሀገራት ቡናው ከደን ጭፍጨፋ ንክኪ የጸዳ ስለመሆኑ በመረጃ የሚታገዙበት እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና አከባቢ ጥበቃ ህብረት ስራ መምሪያ ምክትል መምሪያ ኃላፊ እና የቡና ሻይ ቅመማ ቅመም ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሪት ወርቅነሽ ባድንስ በበኩላቸው ዞኑ ከ160 ሺ ሄክታር በላይ የቡና ሽፋን እንዳለው ጠቁመው ከዚ ውስጥም 135 ሺ ሄክታር ምርት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ያቀረበው ከደን ጭፍጨፋ እና ውድመት ውጪ የሚገኝ ቡና ለመግዛት ያቀረበው መስፈርትም በዞኑ ይደርስ የነበረው የቡና ጥራትን ችግር ከመቀነሱ ባለፈ ይታይ የነበረውን የደን መመናመን ችግር ይቀንሳል ብለዋል።

በተመሳሳይም የምእራብ ኦሞ ዞን ቡና ሻይ ቅመማ ቅመም የምርት ዝግጅት ባለሙያ አቶ ትእግስቱ ወንድሙ በበኩላቸው ለቡና ምርት ጥራት ማነቆ የሆነው ምርቱ በተለያዩ ምክንያት ይባክን እንደነበር አውስተው ይህ ስልጠና የዞኑን የቡና ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ ያስችላል ብለዋል።

በስልጠናው የተሳተፉ ተሳታፊዎችም የቡና ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ጥራቱንም ለማስጠበቅ ስልጠናው አጋዥ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን