”ባላ ካዳቤ ”
በማቴዎስ ባሩ
የጊዲቾ ብሔረሰብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ከሚገኙ ሦስቱ ነባር ብሔረሰቦች አንዱ ሲሆን ብሔረሰቡ በርካታ የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነው። የዘመን መለወጫ “ባላ ካዳቤ” በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው በዓል ነው። የዘመን መለወጫ “ባላ ካዳቤ” በዓሉን የሚያከብረው አዝመራው ከተሰበሰበ በኋላ ነው።
በጊዲቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ ተደርጎ የሚከበር ነው ባላ ካዳቤ ። ”ባላ ካዳቤ” የሚለው ሐረግ ከሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው ። በመሆኑም ባላ ካደቤ ”baala kadabee” ትርጉሙ የብርሃን በዓል ማለት ሲሆን ከክረምት ወደ በጋ ማለትም ከጨለማ ወደ ብርሃን መሸጋገሪያ፣ የአብሮነትና የፍቅር፣ የመቻቻልና የመተሳሰብ በዓል ነው። የበዓሉን መቃረብ የሚያበስሩ በአካባቢው መጠሪያ ሶምቦሎልቴ ‘sombolooltte’ የሚባሉ ወፎች መታየት ሲጀምሩ ፣ ምድሪቷ በአበቦች ስታጌጥ እና መሰል የተፈጥሮ ምልክቶች መታየት ሲጀምሩ “ባላ ካዳቤ” በዓል መድረሱን እንደሚገነዘቡ የብሔረሰቡ ተወላጆች ይገልፃሉ ።
“የባላ ካዳቤ” በዓል መቃረቡን ተከትሎ ህፃናት ”sombolooltte soo yaadde, baala aamine soo yaadde, sombolooltte soo yaade shore aamine soo yaadde,… ማለትም ሶምቦሎልቴ ሥጋ አስታወሰችን ፣ ሶምቦሎልቴ ገንፎ እንድንበላ አሳሰበችን…ወዘተ በማለት ለወራት ያክል በተከታታይ ወፎቹ ሲበሩ የሚያሳዩትን የሦስት ማዕዘን ቅርፅ እየሠሩ ህፃናት በመስካቸው በማዜም ይጫወታሉ ።
በብሔረሰቡ ለዚህ በዓል ሁሉም አባወራ ፣ እናቶች ፣ ወጣቶችና ህፃናትም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው ።
የአባቶች ሚና ለዓመት በዓል አስበው የቁጠባ ሂደቶችን ሲያከናውኑ ይቆያሉ ። በንጉሡ ወይም በዎኖ አማካይነት በተሰጠው ቡድን ወይም ማራንቻ አባቶች በአጠቃላይ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የማሟላት ኃላፊነት ይወጣሉ ።
የሴቶች ሚና በተመለከተ ደግሞ ለበዓሉ ከሁለት ወራት አስቀድሞ የማገዶ እንጨትና ለባህላዊ መጠጥ(ጠላ) ብቅል ያዘጋጃሉ፣ እህል እየፈጩ ዱቄት ያጠራቅማሉ፣ ቆጮ እየቆረጡ ያሰናዳሉ፣ ቅቤ ፣ ቡላ ፣ ዳጣና የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ያዘጋጃሉ ።
ወጣት ወንዶች ደግሞ ከሸማ የሚሠራ መቀነት( hiitu)፣ ማበጠሪያ (fufo ) ጨምሮ ሌሎችን ለልጃገረዶች ያሟላሉ ። ለባህላዊ ጭፈራ የሚሆን ረጅም ቀጭን በትር /Dama/ እና ችቦ ወይም Dab ያዘጋጃሉ፤ ከወላጆቻቸው የሚሰጡ ተጨማሪ ትዕዛዛትንም ይፈጽማሉ ።
ልጃገረዶች የማገዶ እንጨት ሰብስበው ይከምራሉ፡፡ከተለፋ ቆዳ በዛጎል አሸብርቆ የሚሠራ ሴቶች በወገባቸው የሚያገለድሙትን “hampala” የሚባል ጌጥ ያዘጋጃሉ ፡፡ የቤተሰብ ልብስ ያጥባሉ፣ የቤታቸውን ግድግዳውን በአመድና ጥቅርሻ በተለያየ ስዕላ ስዕል ማስዋብ ወዘተ… ያከናውናሉ ።
በበዓሉ ሰሞን ተጣልተው የከረሙ ግለሰቦች ይታረቃሉ ፤ በበጋው ወቅት የተዳሩ ሙሽሮች ይወጣሉ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ከጎረቤቶቻቸውና ከዘመድ አዝማድ ስጦታ ”ilabo” ይቀበላሉ ፤ ይጫወታሉ ፤ ይደሰታሉ ።
በዋዜማው ቀን ምሽት ሁሉም ቤት የበዓል ገንፎ ”ሾሬ ካባላ” shore kabaala ይበላል ።
ወቅቱ ሲደርስ የባላ ካዳቤ እርድ በጎሳ መሪዎች እና ሽማግሌዎች ዋስትና በበጋ ጊዜ ማለትም በጥር ወር በሚከፈል ገንዘብ በሬ ያለው ግለሰብ እንዲያዘጋጅ ስምምነት ተደርጎ በእርዱ ቀን ያለ ቅድመ ክፍያ በሬ ይቀርባል።
በበዓሉ ዕለት ማለዳ አባቶች በሶንጎን በየጎሳው መሪ አማካይነት ለበዓሉ የተዘጋጀውን በሬ ያርዳሉ ፤ እዚያው በዓመቱ ተረኛ የሆነ ግለሰብ ከቤቱ ዳጣ ፣ ቅቤ፣ ጠላና ቂጣ ወይም እንጀራ ያቀርባል በጋራ ይቃመሳሉ ።
ወደየቤታቸው ከተመለሱም በኃላ በታላላቆቻቸው ቤት በዓመት በሠላም ያደረሰላቸውን ፈጣሪ እያመሰገኑ በጋራ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ።
ከዚህ በኋላ ጀንበሯ ልትጠልቅ ሲትቃረብ ችቦ በጎሳ መሪው ይለኮሳል። ሁሉም ወንዶች ከየቤታቸው ችቦአቸውን ይዘው በመውጣት በሥርዓቱ መፈጸሚያ ሥፍራ በመሄድ በአንድ አድባር ይደምራሉ። እዛው ክብ ሠርተው እየዘፈኑ ይጨፍራሉ። ከዚያም እየተጫወቱ ወደ ሰፈር ይመለሳሉ። በዕለቱ መገባበዝ፣ አብሮ መብላትና መጠጣት የተለመደ ነው። አካባቢው በደስታ ይጥለቀለቃል ። በዚህ አጋጣሚ እጮኛሞቹ የሚተዋወቁበትና መተጫጨቱ የሚጸናበት ነው። ተሞሽራ የቆየችውም ቅቤ ተቀብታ በባህላዊ ልብሶች አሸብሪቃና ተውባ ወደ አደባባይ ወጥታ ትታያለች።
ባላ ካዳቤ(baala kadabee)ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የብሔረሰቡ ማንነት መገለጫ ነዉ ። የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የአዲሱ ዓመት የመሸጋገሪያ በዓል የሆነው ”ባላ ካዳቤ” በውስጡ በርካታ ባህላዊ ዕሴቶች ያሉበት በመሆኑ በጥናትና ምርምር ተደግፎ በቱሪዝም ዘርፍ የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ዛሬም ትኩረትን ይሻል ።
የብርሃን፣ የአንድነት፣ የዕርቅ፣ የፍቅርና የሰላም ተምሳሌት የሆነው ”ባላ ካዳቤ” በዓል ባህላዊ አስተዳደርን፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፀጋዎችን በውስጡ አቅፎ ያየዘ በብሔረሰቡ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው በዓል ነው ።
ዘንድሮ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተመርቆ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ደስታቸውንና ምስጋናቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት በመሆኑ የበዓሉን አከባበር ልዩ ያደርገዋል ።
”ባላ ካዳቤ”ን ጨምሮ የብሔረሰቡን ቋንቋ፣ ታሪክና ባህላዊ ዕሴቶችን በመጠበቅ፣ በመንከባከብና በማልማት ለቀጣይ ትውልድ በማሸጋገር ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው አንደሚገባ የብሔሩ ተወላጆችና ምሁራን ይናገራሉ ።
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም
ጃፓን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ብራዚልን አሸነፈች
ከተሞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው አገልግሎት መሥጠታቸው የተገልጋይና የአገልጋይ ግንኙነት ጤናማና እርካታ የተሞላበት እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ