ሀዋሳ፡ ግንቦት 25/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኦሞ ባንክ አርሶ አደሩን እና በተለያዩ የንግድ የስራና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ የህበረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን በካፋ ዞን የኦሞ ባንክ ጠሎ ቅርንጫፍ አስታውቋል።
ባንኩ የአሰራር ስርዓቱን በማዘመን የደንበኞችን ቁጥር እያሳደገ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በጠሎ ወረዳ የኦሞ ባንክ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰጋኸኝ አበበ እንደገለጹት፤ ባንኩ ወደ ባንክ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ለአካባቢው ማህበረሰብ የብድር አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን የኢኮኖሚ ችግር ሲቀርፍ ቆይቷል።
በአሁን ወቅት ባንኩ ከብሄራዊ ባንክ በተሰጠው ፈቃድ መሰረት የአሰራር ስዓቱን በማሻሻል በባንክ በመደራጀት ከብድር ስርጭት በተጨማሪ ደንበኞች በባንኩ እንዲቆጥቡና ገንዘብ እንዲያንቀሳቅሱ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ባንኩ በተያዘው በጀት አመት ከ1መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ማስጠቆብ መቻሉን የገለፁት ሀላፊው ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት መስጠት መቻሉንም ገልፀዋል።
በድለባ፣ በከተማ ግብርናና በተለያዩ የንግድ ስራዎች ለተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ባንኩ የብድር አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጹት አቶ አሰጋኸኝ ከዚህ ቀደም ከተቋሙ የብድር አገልግሎት ወስደው ያልመለሱ ማህበራት የወሰዱትን ብድር የማስመለስ ስራ በወረዳው ከተቋቋመው ግብረ-ሃይል ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም ከ10 ሚልዮን ብር በላይ ማስመለስ የተቻለ ሲሆን ይህ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል አቶ አሰጋኸኝ።
የባንኩ ደንበኞች በበኩላቸው ባንኩ ባደረገው ማስተካካከያ መደሰታቸውን በመግለጽ ከቁጠባ በተጨማሪ ከባንኩ የብድር አገልግሎት በማግኘት ኑሯቸውን ለማሻሻል ማቀዳቸውን ነው የገለፁት።
ባንኩ ለአርሶ አደሮችና ለወጣቶች የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ሥራ አጥነትን በመቀነስና ቁጠባን ባህል በማድረግ ረገድ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ትዕግስቱ ጴጥሮስ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 25 ሺህ 338 ሊትር ቤንዝልና 62 ሺ 686 ሊትር ናፍጣ በቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፍትህና የጸጥታ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ
ከአየር ንብረት ተፅዕኖ ጋር እየተስተዋሉ ያሉትን ችግሮች ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ