ሀገራዊ ልማትና ዕድገትን የሚፈታተኑ ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነትን በተደራጀ ሁኔታ መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ

ሀገራዊ ልማትና ዕድገትን የሚፈታተኑ ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነትን በተደራጀ ሁኔታ መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 20/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ምክትል ርዕሰ መሰተዳደር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ሀገራዊ ልማትንና ዕድገትን የሚፈታተኑ ሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነትን በተደራጀ ሁኔታ መከላከል እንደሚገባ ገለጹ፡፡

የወጣቶችን ሥራ ዕድል ፈጠራ በማጠናከርና በማጎልበት የክልሉን ቁሳዊና ሰብአዊ ጸጋዎች ሥራ ላይ ማዋል ይገባል ተብሏል፡፡

የሀገሪቱን ዕድገትና ልማት የሚፈታተኑ ወቅታዊና ሥር የሰደዱ ድህነትና ሥራ አጥነትን ለማስወገድ እንዲቻል የተደራጀ የሕዝብ ንቅናቄን መፍጠርና መምራት ይገባል በማለት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገልጸዋል፡፡

ከነዚህ ችግሮች ጋር በተያያዘ የኑሮ ውድነት ደግሞ የሰፊውን ማህበረሰብ ቤት እያንኳኳ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የፍጆታ ምርቶችን ማረጋጋት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

በርካታ የሥራ ዕድል ያላገኙ ወጣቶች በክልሉ መኖራቸውን ገልጸው የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ደግሞ ብዙ አማራጮች ያለበት መስክ በመሆኑ ወጣቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በተቀናጀ ሁኔታ መመራት አለበት ብለዋል፡፡

በሌማት ቱሩፋት የተጀመሩ ነገሮች ተስፋ ሰጪ በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ አማካይነት የተዘጋጀው ለአምስት ወራት የሚቆይ ክህሎት መር የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ የሕዝብ ንቅናቄ ሰነድ ቀርቦ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

ክልሉ ያልተጠቀመባቸውን በርካታ ቁሳዊና ሰብአዊ ጸጋዎችን ለመጠቀም እንዲቻል በክህሎት የተደገፉ ሥራዎች መሰራት እንዳለበትም ተመልክቷል፡፡

በገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ በካፋ ዞንና በሌሎች ዞኖችም ወደ ተግባር የተገቡ እንቅስቃሴዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

በከተማ ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ የተመጀሩ ሥራዎችም ትኩረት መደረግ እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡

ክልሉ ወደ 33 ሚሊዮን ብር አውጥቶ የገዛቸው ማሽኖችም በተቀናጀ ሁኔታ ሥራ ላይ እንዲውሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት በተጠናከረ ሁኔታ ማከናወን ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡

በቀጣይ የዶሮ ዕርባታን ጨምሮ ትኩረት ተደርጎ በሚሰሩ የልማት ዕቅዶች ላይ የውይይቱ ተሳታፊዎች መክረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ መለሰ ገብሬ – ከቦንጋ ጣቢያችን