የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት ከማስደገፍ በተጨማሪ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረጉ ለሌሎችም ተቋማት እንደ አርአያ የሚወሰድ ነው – ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍትህ በኩል የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በጥናት ከማስደገፍ በተጨማሪ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ማድረጉ ለሌሎችም ተቋማት እንደ አርአያ የሚወሰድ ነው ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ ገለፁ።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሀይማኖት አባቶችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ በሚዛን አማን ከተማ አካሂዷል።
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ እንደገለፁት፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አገልግሎት አሰጣጡ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ መድረኩን ማዘጋጀቱ ከህዝቡ ጋር በቅርበት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ያሣያል።
ለማህበረሰቡ ቅርብ የሆኑትንና ባለድርሻ አካላትን በማሣተፍ መስራት በአገልግሎቱ ዙሪያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት እንደ አንድ መነሻ ሆኖ እንደሚያገለግልም ተናግረዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በክልሉ ውስጥ የፍትህ አገልግሎትን የተሻለ ቦታ ለማድረስ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን ከመስራቱም በተጨማሪ እንዲህ አይነት የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀቱ ለሌሎች ተቋማት እንደ አብነት ይጠቀሳል ብለዋል።
የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ጥላሁን ታደመ በበኩላቸው፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከሀገር ሽማግልዎች፣ ከሀይማኖት አባቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መደረጉ የፍትህ አሰጣጡን የተሻለ ቦታ ለማድረስ አቅም እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
ለምክክር መድረኩ መነሻ ይሆን ዘንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን የዘጠኝ ወራት የስራ እቅድ አፈፃፀም ያቀረቡት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ 2 ሺህ 447 መዝገቦች ውስጥ 2 ሺህ 289 መዝገቦች ውሳኔ በመስጠት 158 መዝገቦች በአራተኛው ሩብ አመት በማሸጋገር የእቅዱን ከ93 በመቶ በላይ ማከናወን እንደተቻለ አብራርተዋል።
ይህ ተግባር ከባለፈው አመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ14 በመቶ በላይ ብልጫ ማሣየቱን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሚቀጥለው አመት ተግባራዊ የሚደረግ መነሻ እንዳለ ሆኖ እስከአሁን ባለው አሰራር ፍትህን በሁለት ወር ለመወሰን በተቀመጠው ግብ መሠረት ውሳኔ ካገኙ 2 ሺህ 289 መዝገቦች ውስጥ 2 ሺህ 166 መዝገቦች እስከ ሁለት ወር ባለው ጊዜ ውሳኔ በመስጠት 94 በመቶ ማከናውን እንደተቻለ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም በታርጫ ምድብ ችሎት፣ በማሻ፣ በቱም እና በቦንጋ በተዘዋዋሪ ችሎት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በየዘርፉ የተከናወኑ ስራዎችን ያቀረቡት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት በተለይ የፍትሐብሔር ጉዳዮች 152 ቀበሌዎች የባህል ፍርድ ቤቶች በሙከራ ደረጃ በማደራጀት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች ከዳኝነት መፍለስ አንፃር ጉዳዮች መጓተት መኖሩን አንስተዋል።
ፍትህን በአቅራቢያ ለመስጠት ታስቦ ተዘዋዋሪ ችሎቶች መኖራቸው ጥሩ ሆኖ ምድብ ችሎቶችም እንዲጨመሩ ሀሳብ ሰጥተዋል።
ሀሰተኛ ምስክሮች መበራከታቸውን ያወሱት የምክክር መድረኩ የሀይማኖት አባቶች፤ በዚህ ጉዳይ የኛም አሰተምሮት ሊፈተሽ ይገባል ብለዋል።
በጥብቅና ላይ የሚሰሩት ፍርድ ቤቶች ማደር የማይገቡ ውሳኔዎች እንዲያድሩ መደረጋቸው ቀድሞ በጥሩ አፈፃፀም ላይ የነበረው የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአገልግሎት አሰጣጡ ችግር ውሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
በተነሡ ጥያቄዎች ላይ የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎችና የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ምላሽ ሰጥተዋል።
በምክክር መድረኩ ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፤ የህዝቡን የፍትህ ጥያቄ በጥራትም በፍጥነትም በቅርበትም ለመስራት ትኩርት መደረጉን ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ አሣሣኸኝ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በቋሚነት የሚደገፉበት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቡርጂ ዞን አስተዳደር አስታወቀ
“አንድ ሰው ወደዚህች ምድር ሲመጣ እንዲሰራ የተፈቀደለትና የሚጠበቅበት ነገር አለ” – ታደሰ ገብሬ /ጃክሰን/
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ