በተያዘው 2017 በጀት አመት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ከ1.1 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የሀላባ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

በተያዘው 2017 በጀት አመት የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ከ1.1 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የሀላባ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ

የመንግስትን ግብር በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።

ገቢ የሀገርን ልማትና እድገት ለማፋጠን መሰረት በመሆኑ እንደ ሀገር በዘርፉ የማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ የገቢ አቅምን ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጭዎች የሀገርን ልማት እና ዕድገት ለማፋጠን ግብር ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

ዞኑ የሚያመነጨውን የገቢ አቅም በተገቢው ለመሰብሰብ በተደረገው እንቅስቃሴ በተያዘው 2017 በጀት አመት ባለፉት 6 ወራት ከመደበኛና ማዘጋጃ ቤቶች በአጠቃላይ ከ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 1 ቢሊየን 139 ሚሊዮን 272 ሺ 994 ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን የሀላባ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጤ ዮሐንስ ገልፀዋል።

በዘርፉ የተደረገውን የግብር ማሻሻያ ተከትሎ የአመቱን ጥቅል ገቢ ከፍ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ወይዘሮ ፋጤ ተናግረዋል።

የገጠር መሬት ገቢ አሰባሰብን ጨምሮ ከአዲሱ የግብር ማሻሻያ ጋር በተያያዘ በተሳሳተ መልኩ የሚነሱ የግንዛቤ ክፍተቶችን ለማረም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በተለያዩ አማራጮች እየተሰራ መሆኑንም ኃላፊዋ ጠቁመዋል።

በዞኑ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን የተጀመረውን የአሰራር ማሻሻያ ስራ ይበልጥ አጠናክሮ በመቀጠል የኪራይ ሰብሳቢነትን ለመከላከል ክፍያን በሲስተም ለመፈጸም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በአዲሱ ገጠር መሬት አጠቃቀም መመሪያ ማሻሸያን ተከትሎ የዘንድሮ ግብር ክፍያ መጠን ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመስማት ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ከዚህ በፊት የነበረው የገጠር መሬት ግብር አነስተኛ ሄክታር መሬት እና ከፍተኛ ሄክታር መሬት ያለው የሚከፈለው ክፍያ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በአዋጅ እና በመመሪያው ላይ የማሻሻያ እርምጃ መወሰዱንም አመላክተዋል።

ህብረተሰቡ በንግዱ ዘርፍ ዕቃዎችን ሲገዛ ደረሰኝ የመቀበል ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ በአማርኛ እና በሀላብኛ ቋንቋ የተዘጋጁ መልዕክቶችን በማስተላለፍ፣ በአዲሱ የገጠር መሬት ግብር አዋጅ እና ደንብ ማሻሻያ ዙሪያ በሁሉም አካባቢዎች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መሰራታቸውን የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ ሁሉም ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በተገቢው በመክፈል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ: ሙዘይን ሰኒ – ከሆሳዕና ጣቢያችን