የዳውሮ ብሔር ባህልና ታሪክ ሳይበረዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 03/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዳውሮ ብሔር ባህልና ታሪክ ሳይበረዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ይበልጥ መስራት እንዳለባቸው ተገለፀ፡፡

የዳውሮ ብሔር ዘመን መለወጫ “ቶኪ-በኣ” በዓልን ምክንያት በማድረግ በተካሔደው የፓናል ውይይት፥ የዳውሮኛ ቋንቋ ይበልጥ ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮ ላይ የተለያዩ ጥናታዊ ፁሑፎች በባህሉ አዋቂዎች ቀርቦል።

በቋንቋው አጠቃቀም ዙሪያ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶክተር መንግስቱ ዲናቶ፥ የዳውሮኛ ቋንቋ የራሱ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም ባህሪያት ያሉት ሲሆን ታላላቅ ሰዎችን፣ ነገስታትና የኃይማኖት አባቶችም ተከብረው የሚጠሩበት የራሱ የሆነ የማክበሪያ ቃላት ያለው መሆኑን አመላክተዋል።

ቋንቋው የማህበረሰቡ ማንነት መገለጫም በመሆኑ ይህንን ባህላዊና ታሪካዊ መሠረት ያለውን ቋንቋ ትውልዱ እንዲያውቅና እንዲጠብቅ ማድረግ ያስፈልጋል በማለትም አስረድተዋል።

በመድረክ ከተገኙት ተሣታፊዎች መካከል ዱባለ ገበየሁ፣ አርቲስት ወንድሙ ከበደ እና አቶ አባቴ አይና በቀረቡ ሰነዶች ዙሪያ መጨመር ባለባቸው እና ሊጎለብቱ በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳብና አስተያየት ሰጥተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ የዳውሮ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል “ቶክበኣ” ለአካባቢና ለሀገር የሚሆኑ በርካታ እሴቶች ያለው ሲሆን ይኸውም ከጥንት አባቶች ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው ብለዋል።

የበዓሉም ይሁን ሌሎች ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን በመጠበቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅም በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስብዋል፡፡

በመድረኩ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ ዮሐንስ መካሻ – ከዋካ ጣቢያችን