በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማ እየሆኑ መጥተዋል – በዳዉሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሴክተር ጽ/ቤት

በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማ እየሆኑ መጥተዋል – በዳዉሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሴክተር ጽ/ቤት

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርታማ እየሆኑ መምጣታቸዉን በዳዉሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሴክተር ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የእርባታዉን ዘርፍ በማዘመን በእንስሳት ተዋፅዖ የአካባቢዉን ገበያ ለማረጋጋት በትኩረት እየሰራ መሆኑን በወረዳው ግብርና ጽ/ቤት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሴክተር ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የሎማ ወረዳ በዞኑ ከሚገኙ 11 ወረዳዎች መካከል በእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ፕሮጀክት የሚደገፍ ብቸኛ ወረዳ አንደሆነ ከጽ/ቤቱ ያገኘነዉ መረጃ ይጠቁማል።

በወረዳዉ በዶሮ፣ በዓሣና በወተት ላም እርባታ እንዲሁም ፍየልና በግ በማሞከት ተደራጅተው ዉጤታማ ከሆኑ ማህበራት መካከል በያሎ ላላ የሚገኝ አናኒያ የወተት ላም ህብረት ሥራ  ማህበር እና ደነባ ዚማ ሠላም የዓሳ አስጋሪ ህብረት ሥራ ማህበር የሚጠቀሱ ናቸዉ።

የአናኒያ ማህበር አባላት ራሳቸዉን ከመቻል ባለፈ በእንስሳት ተዋፅዖ ገበያ ለማረጋጋትና አካባቢዉን  ከዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ በምርት ለማስጠራት በሚል ዓላማ ሥራዉን እንደጀመሩ የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ መርክነ ማራ ተናግረዋል።

ማህበሩ 25 አባላትን ያቀፈ ሲሆን በ13 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ላይ 1 መቶ 30 ሺህ ብር  ከመንግስት ብድር ባገኙት ብድር  ወደ 15 ላሞችን  በ135 ሺህ ብር የተሻሻለው ዝርያ ያላቸውን ላሞች በማርባት በአሁኑ ሰዓት  ለያሎና አከባቢ  ከተሞች ወተት እያቀረቡ መሆናቸዉንም  ገልፀዋል።

የወረዳዉ ያሎ ላላ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የግብርና  ባለሙያ  አቶ ዘዉዴ ዘለቀ  ለማህበሩ  ምርታማነት ሙያዊ እገዛ እያደረጉ መሆናቸዉን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ከባድርሻ አካላት ሰፋ ያለ የግጦሽ ቦታና የፋብሪካ ተረፈ ምርት  የሚያገኙበት መንገድ ቢመቻችላቸዉ ለአከባቢዉ ዕድገት ትልቅ አስተዋፅዖ  የሚያበረክት ማህበር እንዳሆነ ተናግረዋል።

ሌላዉ ከ2012  ዓ.ም ሥራ የጀመረዉ የሠላም ዓሣ አስጋሪ ማህበር ሲሆን በወረዳዉ  እንስሳትና ሀብት ልማት ፕሮጀክት በኩል አስፈላጊ ድጋፍ ተደርጎላቸዉ ከቡድን ወደ ማህበር ማደግ  የቻለ  ማህበር ነዉ።

በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ ሰርቶ ከሚያገኘው በየሳምንቱ 3 ሺህ ብር እየቆጠበ ሲሆን በዓመት 1 መቶ 44 ሺህ ብር በመቆጠብ ወደ ዩኒዬን እያደገ ያለ ማህበር ነዉ።

የወረዳዉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ በርገነ ጆርጋ በበኩላቸዉ በ2012 ዓ.ም ጀምሮ በቡድን ከማደራጀት እስከ ማህበር ከ1ሚሊዮን በላይ የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸዉንና ቀጣይም ለማህበሩ እድገት አስፈላጊዉን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

የወረዳዉ  ግብርና  የአከባቢ  ጥበቃና  ህብረት  ሥራ  ጽ/ቤት  ም/ ኃላፊና የእንስሳትና  ዓሳ  ሀብት  ልማት ሴክተር ኃላፊ አቶ መለሰ ክንፈ በእርባታዉ  ዘርፍ  የተደራጁ  በርካታ  ማህበራት  መኖራቸዉን ጠቅሰዉ  ለዉጤታማነታቸዉ  የድጋፍና  ክትትል ሥራ አጠናክረዉ  እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡  አባይነሽ  ወራቦ  – ከዋካ  ጣቢያችን