በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት ለሚደረጉ የኢንዱስትሪ ሽግግሮች ግብርና መሠረት ነው ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪና በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ ተናገሩ
በክልሉ “ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ ለክልላችን ማንሰራራትና ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የግብርና ልማት ሥራዎች ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪና በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ፤ በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት ትኩረት ከተደረገባቸው ሰባት መስኮች ግንባር ቀደም ነው ብለዋል።
በዚህም እንደሀገር ግብርናን መሰረት በማድረግ ለሚደረገው የኢንዱስትሪ ሽግግር በመደመር መንግስት ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በልዩ ትኩረት መደገፍ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የመደመር መንግስት በቀጣይ ከ65 በመቶ በላይ በስራ ዕድል ፈጠራ ካስቀመጣቸው ዕቅዶች የግብርናው መስክ የሚሸፍን እንደሆነም አቶ ተክሌ አንስተዋል።
መንግስት በተለይም ባለፉት ቅርብ ዓመታት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በሌማት ትሩፋት፣ በግብርና መር ገጠር ትራንስፎርሜሽንና ተያያዥ መስኮች ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎችን በአግባቡ በመደገፍ እንደሀገር በምግብ ራስን ከመቻል አልፎ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ በክልሉ ባለፉት አራት ዓመታት የግብርና ምርታማነትን በማረጋገጥ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተደረጉ ጥረቶች ለውጥ እያስመዘገቡ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም በዋናነት ከዚህ ቀደም የተለመደውን የአዝመራ ወቅት በማሻሻል የበጋ መስኖ ስራዎች ላይ የተደረጉ ትኩረቶች አጋዥ እንደነበሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
በክልሉ 93 የመስኖ አውታሮች እንደሚገኙ ያነሱት አቶ ማስረሻ፤ እነዚህንና ሌሎች የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ከአራት ዓመት በፊት 433 ሄክታር የነበረውን የበጋ ስንዴ ልማት በ2018 ዓመተ ምህረት ወደ 5 ሺህ 778 ሄክታር በማድረስ የምርት መጠን ወደ 190 ሺህ ኩንታል ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
በሆርቲካልቸር ልማት በ2018 በጋ አዝመራ 156 ሺህ ሄክታር በማልማት 28 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የተናገሩት አቶ ማስረሻ፤ በዘንድሮው አዝመራ 162 ሺህ ሄክታር በማልማት ከ35 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በመደበኛ በልግ፣ በሌማት ትሩፋት፣ ቡናና ቅመማቅመም ምርቶች በክልሉ በበጋ አዝመራ በልዩ ትኩረት የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በተለይ አርሶና አርብቶ አደሩ እነዚህን በአግባቡ ማከናወን እንዲችል የተሻሻሉ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ለማሸጋገር የአርሶ አደር ሰርቶ ማሳያዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አንስተው በመስኩ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት ይጠበቃል ብለዋል።
በክልሉ “ምርትና ምርታማነትን ማረጋገጥ ለክልላችን ማንሰራራትና ከፍታ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው ክልል አቀፍ የግብርና ልማት ሥራዎች ንቅናቄ መድረክ የክልሉ አስተባባሪ አካላትን ጨምሮ ከሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
ዘጋቢ፣ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
ምክር ቤቱ በህዝቡ ህይወት ላይ የሚታይ ለውጥ ለማምጣት እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ካሰች ኤሊያስ ገለጹ
የኩታ ገጠም የአስተራረስ ስርአትን በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ማዘመንና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ገለፁ
“የዘመነ ክህሎት ስነ ምህዳር ለዘላቂ ስራ እድል” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው