በካፋ ዞን “ማንሰራራት ለዞናችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የመደመር መንግስት የትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው

በካፋ ዞን “ማንሰራራት ለዞናችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የመደመር መንግስት የትውውቅ መድረክ እየተካሄደ ነው

“ማንሰራራት ለዞናችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል የካፋ ዞን የመደመር መንግስት ትውውቅና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ምክክር የሚደረግበት መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በትውውቅ መድረኩ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሤ ወልደጊዮርጊስ፤ አዲሱ የመደመር መንግስት ዋና ተልዕኮ የህብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻል ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር ከትላንት መልካም ነገሮችን በመውሰድ ጉድለቶች በማረም ነገን በጠራ ራዕይ መጓዝ የሚያስችለው የመደመር እቅድ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

አመራሩ “ጊዜ የለንም!” በሚል መንፈስ ተግባራትን መፈፀም እንዳለበት ተናግረዋል።

ህዝቡን ለማገልገል ዕድል ማግኘት መታደል የሚሆነው በተሰማራንበት ዘርፍ ውጤት ማስመዝገብ ስንችል ነው ያሉት አቶ ንጉሤ፤ ይህን ለማሳካት ጥረትና ትጋት ማደረግ እንደሚገባ አበክረዋል።

መድረኩ በዞኑ በየደረጃው ያለው አመራር ህዝብን አስተባብሮ የልማት ተግባራትን በብቃት በመምራት፣ በተሻለ አፈጻጸም ለላቀ ውጤት ለማብቃት የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ 

የአመራርነት ዓላማ አገልግሎት መሆኑን ገልጸው፤ የአገልግሎት መገለጫ ውጤት በመሆኑ አመራሩ ተግባሩን በጊዜ የለንም መንፈስ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የካፋ ዞን መንግስት ዋና ተጠሪና የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጋዎ አባመጫ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ ሀገራችንን ወደ ብልጽግና ማማ የማሻገር ተልዕኮ የተሸከመ የሀሳብ ባለቤት የሆነ ፓርቲ ነው ብለዋል።

የሚገጥሙንን ተግዳሮቶች ወደ ድል በመቀየር ምክንያቶችን በማጥናትና በመተንተን በሁሉም መስክ ለውጤት መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የውይይት መድረኩ አዲስ የአመራር ባህል፣ የስራ መንፈስ፣ የአፈፃፀም ስርዓትና የውጤት ታሪክ ለማስጀመር ያለመ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ጋዎ፤ ውጥኖች እንዲሳኩ ህብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ ፈጠነ ወንድሙ – ከቦንጋ ጣቢያችን