አዲሱ የካቢኔ ስብጥር ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን በተግባር ያሳየ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
ኢዲሱ የካቢኔ ስብጥር ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን በተግባር ያሳየ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረቡ የመደመር መንግሥት የካቢኔ አባላት ሹመት ተቀብሎ አፅድቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲሱ የካቢኔ አባላት ስብጥር በሀይማትም፣ በፆታ እና ከብሔር አንፃር ሚዛኑን እንዲጠበቅ በማድረግ ኢትዮጵያ የሁሉም መሆኗን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዓመታ ከሀረሪ ክልል አንድም በሚኒስትር ደረጃ የተሾመ ሰው እንዳልነበር በማሳያነት ጠቅሰው፤ በመደመር መንግሰት የተደረገው ሹም ሽር አዲስ መንገድ የከፈተ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
አዲስ የተሾሙ የካቢኔ አባላት መሻታችን ሰፊ፣ የሰለጠነችና የዜጎቿን ተጠቃሚነት የምታረጋግጥ፣ ሁሉም ዜጋ የኔ ናት የሚላትን ኢትዮጵያ መገንባት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የካቢኔው ስብጥር ከብቃትና ልምድ ባሻገር የሕብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን ገጽታ እንዲያንፀባርቅ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ጠቁመው፤ የብሔር፣ የጾታ እና የእምነት ስብጥርን ሚዛን በጠበቀ መልኩ እንዲዋቀር መደረጉን አስረድተዋል፡፡
አደጉ በሚባሉ ሀገራት ጭምር ዘጠኝ ሴት ሚኒስትሮች የላቸውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ሴቶች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት አርዓያ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል፡፡
አያይዘውም በሀገራችን ኢትዮጵያ ማንም አንደኛ ማንም ሁለተኛ የሚባልበት ዘመን ማብቃቱን ገልፀው፤ በጋራ ሀገር እንገነባለን ከዚህ ውጪ ያለው የእኔ እበልጥ አካሄድ በየትኛውም ተቋም ውስጥ ተቀባይት እንደሌለውና ውድቀትን እንደሚያመጣ አስገንዝበዋል።
አዲስ የተሸሙት የመደመር መንግስት የካቢኔ አባላት በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ካሡ ብርሃኑ

More Stories
ዕጩ የካቢኔ አባላት ከወትሮ በተለየ መንገድ ባለዕዳና ከፍተኛ አደራ የተጣለባቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ ማሳሰብ እወዳለሁ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ሹመት የምንዝናናበት ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማፅናት እና ለማበልፀግ የምንሰራበት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው በሙሉ ድምጽ ጸድቋል