በበጀት ዓመቱ ከ38 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው – የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት

በበጀት ዓመቱ ከ38 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ ነው – የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት

በ2019 በጀት አመት ከ38 ሺህ ቶን በላይ የታጠበ እና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

‎ጥራቱን የጠበቀ እና የተረጋጋ የቡና ምርት ግብይት እንዲከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባም ተጠቁሟል።

‎በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ በቡና የተሸፈነ ሲሆን ዞኑ በጥራትም ሆነ በብዛት ከፍተኛ መጠን ያለውን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብ ይታወቃል።

‎በ2018 በጀት አመት የቡና ምርታማነት በአንድ ሄክታር 9 ነጥብ 7 ኩንታል የነበረው በ2019 በዞኑ በሚገኙ በሁሉም መዋቅሮች የተሻለ የቡና ምርታማነት በመኖሩ 11 ነጥብ 19 ኩንታል በሄክታር ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

‎የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አማኑኤል ወርቁ እንደተናገሩት÷ በ2018 በጀት አመት በቡና ግብይት ሂደት ላይ የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን በመገምገም በ2019 የትኩረት አቅጣጫ ላይ በዞኑ ከተቋቋመው ከቡና ቁጥጥር ግብረ ሃይል ጋር በመግባባት ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል።

‎በያዝነው በጀት አመት ከአየር መዛባት ጋር በተያያዘ የዝናብ እጥረት እንደነበር ጠቅሰው፤ በቡና ምርት ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢያደርስም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው በመስራታቸው ዘንድሮ የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

‎በበጀት ዓመቱ 137 ሺህ 367 ቶን እሸት ቡና ለመሰብሰብ አቅደው እየሰሩ መሆኑን ኃላፊው ገልፀው፤ ከዞኑ 38 ሺህ 481 ቶን በላይ የታጠበና ያልታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡

ዕቅዱን ለማሳካት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በተዘጋጀው ማዕከል ብቻ የቡና ግብይት እንዲፈጸም በዘርፉ ከተቋቋመው ግብረ ሃይል ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

‎ጥራቱን የጠበቀ እና የተረጋጋ የቡና ምርት ግብይት እንዲፈጸም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊው፤ አላስፈላጊ የግብይት ሂደት እንዳይከናወን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

‎ዘጋቢ፡ እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን