የሀገራችንን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ
የሀገራችንን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በሀድያ ዞን ሶሮ ወረዳ በ114 ሚሊዮን ብር ወጪ 11 ቀበሌያትንና 2 ከተማ አስተዳደሮችን የሚያገናኝ 36.97 ኪሎ ሜትር የመንገድ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለምረቃ በቅቷል።
በመንገድ ምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትልና የሁሉ አቀፍ ገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማቴዎስ ሎምበሶ፤ የህዝቡን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ (የሪካፕ) የገጠር መንገድ ትስስር ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ2017 ዓ.ም መጀመሩንና በክልሉም በመጀመሪያ ዙር በስምንት ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉን አብራርተዋል።
የሶሮ ወረዳ በፕሮግራሙ የመጀመሪያው ዙር ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አንዱ መሆኑን ያነሱት አቶ ማቴዎስ፤ በወረዳው በፕሮግራሙ አራት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የመገንባት ስራዎችን በማከናወን ሶስቱ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ከወሼባ ጎርጣ አሼ ግራራሞ የ11 ነጥብ 94 ኪሎ ሜትር፣ ከጊምቢቹ ቀጫ ጃጁራ 13 ነጥብ 83 ኪ.ሜ እንዲሁም ከጊምቢቹ ሁለተኛ ኦዳ የፌደራል አሰፓልት መንገድ 11 ነጥብ 2 ኪ.ሜ በአጠቃላይ 36.97 ኪ.ሜ የመንገድ ፕሮጀክት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን አስረድተዋል።
በሪካፕ ፕሮግራም ለመስራት የታቀደውና በግንባታ ላይ የሚገኘውን የቆሻ 8 ነጥብ 9 ኪ.ሜ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚደረግም ተናግረዋል።
ለምረቃ የበቃው የመንገድ ፕሮጀክቶችም 114 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው እንደሆኑ የገለፁት አቶ ማቴዎስ የመንገድ ዝርጋታው 11 ቀበሌያትን በማገናኘት ለ124 ሺህ 402 የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንደሚሆን አስረድተዋል።
በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ፤ መንግስት ለህዝቦች ልማትን ለማፋጠንና መሰረተ ልማቶችን ለማዳረስ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በከፍተኛ በጀት የተገነባው የመንገድ መሰረተ ልማት ረጅም ጊዜ ማገልገል እንዲችል ማህበረሰቡ ሊንከባከበውና ሊጠብቀው እንደሚገባ ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
የሶሮ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈይሳ ኤርቲሮ በበኩላቸው፤ የተገነባው የመንገድ መሰረተ ልማት የወረዳው ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ከመሆን ባለፈ የማህበረሰባችንን የእርስ በርስ ትስስር የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ዋና አስተዳዳሪው አክለውም ባለፈው በጀት አመት በወረዳው የተሰራው የመንገድ መሰረተ ልማት የህብረተሰቡን የዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከመፍታት ባሻገር የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ያስችላልም ብለዋል።
ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመሰራቱ ለበርካታ ችግሮች ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይ መንገዱ ተሰርቶ በመጠናቀቁ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዳቀለለላቸው ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ ረዚቃ ተመስገን – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የየም ብሔር የ2019 የዘመን መለወጫ “ሄቦ” በዓል በዞኑ ሳጃ ከተማ እየተከበረ ይገኛል
“የዲጂታል አጀንዳ እና ሰው ሰራሽ አሰተውሎት ለቱሪዝም አዲስ ቅኝት” በሚል መሪ ቃል የቱሪዝም ቀን በጎፋ እና በወላይታ ዞኖች በድምቀት ተከብሯል
የየም ብሔረሰብ የ2019 ዓ.ም የዘመን መለወጫ የ”ሄቦ” በዓል የተራራቀ የሚገናኝበት የአዲስ ዓመት መጀመሪያ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ አስታወቁ