ሠላምን በማጽናት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ
ሠላምን በማጽናት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የዓለም የሠላም ቀንን በማስመልከት “ለሠላም ያለ ገደብ” በሚል መርህ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ከአርባምንጭ ዪኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቤንኤዘር ተረፈ እንዳሉት፤ ሠላም ለሰው ልጆች ሁሉ መሠረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ለሠላም መሥራት አለበት ብለዋል።
ሠላምን ይበልጥ ለማጽናት በታዳጊ ወጣቶች ላይ በትኩረት መሠራት እንዳለበትም የቢሮ ኃላፊው አንስተዋል፡፡
የአርባምንጭ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ትውልዱ የሠላም ዕሴቶችን አጠናክሮ በመያዝ ለአገራችን ብልጽግና መትጋት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።
ቀኑን አስመልክቶ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የመወያያ ሰነድ ያቀረቡት በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም መምህር እና ተመራማሪ ዶ/ር ያስን ሁሴን እንዳሉት፤ በአገራችን በሁሉም አካባቢዎች የቆዩ የግጭት መፍቻ መንገዶችን አጠናክሮ በመያዝ የሠላም ዕሴቶችን ለማጽናት ሁሉም ወገን በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
አገሪቱ የጀመረችውን የሠላም እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማጽናት የአገር ሽማግሌዎች እና የሐይማኖች አባቶች የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመድረኩ ተሳታፊ ተወካዮች ተናግረዋል።
በመድረኩ ከኬኒያ አጎራባች ዞኖች የተጋበዙ የሥራ ኃላፊዎች በሁለቱ አገራት የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩ ሲሆን የተጀመሩ ሠላምን የማጽናት ጉዳይ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የዓለም የሠላም ቀን በአርባምንጭ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
ዘጋቢ፡ ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የደም ልገሳ ፕሮግራም ህይወትን የማዳን ትልቅ ዘመቻ መሆኑ ተገለፀ
የሸካቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሬ ባሮ” እየተከበረ ነው
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የቱሪዝም ቢሮ 2018 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ እና 2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል