የደም ልገሳ ፕሮግራም ህይወትን የማዳን ትልቅ ዘመቻ መሆኑን የይርጋጨፌ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ጽህፈት ቤቱ የደም ልገሳ ፕሮግራም አካሂዷል።
የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጥላሁን የደም ልገሳ ፕሮግራም ህይወትን የማዳን ትልቅ ስራ መሆኑን ገልፀው፤ አንድ ሰው በሚለግሰው አንድ ከረጢት ደም እስከ ሶስት የሚደርሱ ሰዎችን ህይወት ማዳን እንደሚቻል ተናግረዋል።
ቀይ የደም ሲል በሰውነታችን ውስጥ ለሦስት ወር ብቻ የሚቆይና እራሱን በራሱ የሚተካ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ይህንን ደም በመለገስ በወሊድ ምክንያት ደም የሚፈስባቸው እናቶችንና በተለያየ አደጋ ደም አስፈልጓቸው በህይወትና በሞት መካከል ያሉ ወገኖቻችን መታደግ አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች ጋር አቀናጅተው በመስራት በመጀመሪያ ዙር እስከ 20 ዩኒት ደም ማግኘት መቻላቸውን ገልጸው፤ በዚህ ዙርም ብዙ ሰዎች ደም እየለገሱ መሆናቸውንና ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን መደበኛ ስራችን በመሆኑ አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ ገልፀዋል።
በደም ልገሳ ዘመቻው ላይ ተገኝተዉ ደም ሲለግሱ ያገኘናቸው የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የኢንስፔክሽን እና የስነምግባር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አስቴር በቀቴ፣ የጤና ባለሙያ የሆኑት ስዩም አሳምነውና ሌሎችም ትውልድን እየተካች በደም እጥረት የምትሞት እናት እንዳትኖር ደማችንን በመለገስ ህይወቷን አትርፈን ትውልድን የማስቀጠል ስራ እንሰራለን ብለዋል።
እኛ እያለን አንድም እናት በደም እጥረት ምክንያት መሞት የለባትም ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ በሰውነታችን ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆየውን ደም በመለገስ እናቶች እንታደግ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ ባዩሽ ኢሳያስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የሸካቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሬ ባሮ” እየተከበረ ነው
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የቱሪዝም ቢሮ 2018 በጀት ዓመት የአፈፃፀም ግምገማ እና 2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የምክክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ይገኛል
የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ለግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ምርታማነት ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለፀ