የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው – አቶ መዝረዲን ሁሴን

የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው – አቶ መዝረዲን ሁሴን

በሀገሪቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎትን ለሁሉም ማህበረሰብ ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሪጅን ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከጉራጌ ዞን ከተለያዩ መዋቅሮች ከተውጣጡ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የመሠረተ ልማት አማካሪ አቶ መዝረዲን ሁሴን እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎት በኢትዮጵያም ሆነ በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመሆኑ፤ ይህንን መሠረት ያደረገ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ተደራሽ ለማድረግ የሁሉም አካላት ትብብርና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሀገሪቱ የተጀመረውን የዲጂታል ቴክኖሎጂንና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ውጥኖችን በአግባቡ ተግባራዊ ለማድረግ ጥራቱን የጠበቀ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አቅም መፍጠርና ለሂደቱ የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን መገንባት ወሳኝ መሆኑን አቶ መዝረዲን አመላክተዋል።

በምክክር መድረኩ በክልሉ ያለውን ወቅታዊ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ሂደቶችን የሚያስቃኙ የተለያዩ ሰነዶች ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት እየቀረቡ ሲሆን ሰነዶቹን መሠረተ በማድረግ ውይይቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ የወጣው መርሃ ግብር ያመላክታል።

በምክክር መድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማና ከዞኑ መዋቅሮች የተወጣጡ አመራሮች፣ የሪጅኑ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዘጋቢ፡ አስቻለው ተስፋዬ – ከወልቂጤ ጣቢያችን