የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያና የቀጣይ አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ የሚመክር ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ እያካሄደ ነው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ በጉባዔው መክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት፤ ዜጎች በሀገራቸው ሰርተው እንዲበለጽጉና ከህገወጥ ስደት ተላቀው በራሳቸው አልሚ እንዲሆኑ ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ያለው አስተዋጽኦ ጉልህ ነው።
ስራ አጥነትን ለመቀነስና ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ በእውቀት የተመራ የስራ ዕድል ፈጠራን መጠቀም ወሳኝ እንደመሆኑ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በዚህም ዜጎች በልቶ ከማደር ባለፈ ሀብት እንዲፈጥሩ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፤ በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት 490 ሺህ 270 ስራ ፈላጊዎችን በመለየት ለ464 ሺህ 11 ሰዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የስራ ዕድል መፈጠሩን ነው የገለፁት።
ኃላፊው አክለውም በተቋሙ በሚከወኑ የክህሎት ስልጠና፣ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንና መሰል ተግባራት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ተገቢ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው 314 አዳዲስ ሼዶችን በመገንባትና 375 ከአሠራር ስርዓት ውጭ የነበሩ ሼዶችን ስርዓት ባለው መንገድ ለኢንተርፕራይዞች ማስተላለፍ መቻሉን አቶ ሙስጠፋ አመላክተዋል።
የተለያዩ የፋይናንስ አማራጮችን በመጠቀም ከቁጠባና ከተመለሰ ብድር 1 ነጥብ 56 ቢሊየን ብር ብድር በማሰራጨት የፋይናንስ ችግሮችን ለመቅረፍ በተደረጉ ጥረቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ማስፋት ተችሏል ነው ያሉት።
በክልሉ ዜጎች ካለው አዳዲስና አዳጊ ፍላጎቶች አንፃር ከፋይናንስ አቅርቦት አጥረት መነሻ በብድር ስርጭትም ሆነ የማሽነሪ አቅርቦትና መሰል ችግሮች ማነቆዎች እንደመሆናቸው በቀጣይ በቅንጅት በመስራት መፍታት እንደሚገባ ኃላፊው አመላክተዋል።
በቀጣይ ጠንካራ የስራ ባህል በመገንባት የእሴት ሰንሰለቱን መሠረት ያደረገ የስራ ዕድል ፈጠራን በመከተል ተወዳዳሪና ብቁ ዜጎችን ለመፍጠር መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ለክህሎት መር ስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት በመስጠት በ2019 በጀት ዓመት ለክህሎት 529 ሺህ 974 ስራ ፈላጊዎችን በመለየት ለ450 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተጥሏል።
በየአካባቢው ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ጠንካራ የብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚን የሚያረጋግጡ ስራዎች በቅንጅት ይሰራሉ ሲሉ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ዘርፍ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ እንደመሆኑ ልማታዊ ወጣቶችን ለመፍጠር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
የነገ ትልልቅ ኢንዱስትሪያሊስቶችን መፍጠር ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ግንባታ የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ ሁሉም በዚህ ዘርፍ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በ2019 ተቋሙ ወደ ተሻለ አቅም ማደግ እንዲችል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ላይ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም በቁጭት ወደ ስራ መገባት አለበት ነው ያሉት ዶክተር ንጉሴ።
በመድረኩም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ንጉሴ አስረስ(ዶ/ር)ን ጨምሮ አቶ ታመነ ገብሬ በክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ የመሰረተ ልማትና የመንግስት ሀብት ቁጥጥር ቦርድ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ የክልል ማዕከል ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም የክልሉ ካቢኔ አባላት እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛል።
ዘጋቢ:- አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ ነው – አቶ መዝረዲን ሁሴን
ታላቁ የጊፋታ ዋዜማ የሩጫ ውድድር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሄደ
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ቴክኖሎጂን በመቅዳት፣ በማሻሻልና በመፍጠር ለሀገራዊ ዕድገት ከፍተኛ አበርክቶ አላቸዉ – የክልሉ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰፋ ደቼ