የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአቅመ ደካማ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ሀዋሳ፡ ጳጉሜን 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ በሀዌላ ወረዳ ለሚገኙና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ዛሬ የኅብር ቀን በክልሉ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ መሆኑን አንስተው በ2019 የትምህርት ዘመን ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች 60 ሺህ ደርዘን ደብተሮችና ከ3 ሺህ በላይ እስኪርቢቶዎች ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

እንደ አቶ በየነ ገለጻ፤ የተማሪዎችን ትምህርት ለመደገፍ የትምህርት ቁሳቁስ ከማቅረብ ባለፈ በክልሉ የተለያዩ ማኅበራዊ ተግባራትም እየተከናወኑ ነው።

ከእነዚህም መካከል የማዕድ ማጋራት፣ የደም ልገሳና ሌሎች የበጎ ፈቃድ ተግባራት ይገኙባቸዋል ብለዋል።

እነዚህ ተግባራት በክልሉ የመረዳዳት፣ የመተባበርና የማኅበራዊ ኃላፊነት ባህልን ለማጠናከር የሚያግዙ መሆናቸውንም አቶ በየነ ጠቁመዋል።

በተለይም አቅመ ደካማ ተማሪዎችን በትምህርት ቁሳቁስ መደገፍ ተማሪዎቹ በቁሳቁስ እጥረት ሳቢያ ከትምህርት እንዳይርቁ ከማገዝ ባለፈ በትምህርት ዘርፍ የእኩል ዕድል ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ የትምህርት ጥራትን የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ድንቅነሽ ደግፌ፤ ዘንድሮ የክረምት በጎ ስራን በማስተባበር በስፋት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል።

የዘንድሮውን የበጎ ሥራ ልዩ የሚያደርገው ባለሀብት፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉም ድጋፍ ማድረጋቸው ነው ብለዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ተመስገን ንጉሴና ተማሪ ምህረት ጌቱ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ ታሪኳ በቀለ