ብዝሃነታችን የማንነታችን ጌጥ እና የአብሮነታችን ከፍታ ነው ሲል የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ
ሀዋሳ፡ ጳጉሜ 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ብዝሃነታችን የማንነታችን ጌጥ እና የአብሮነታችን ከፍታ ነው ሲሉ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ ገለፁ።
”ብዝሃነት የኢትዮጵያ ጌጥ” በሚል መሪ ቃል ጳግሜ 4 የህብር ቀን በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ ኢትዮጵያውን የተለያየ ባህል፣ ቋንቋ ፣ ታሪክ፣ ወግና እሴት ያለን ከመሆኑ በተጨማሪ ከሁሉም አለም በተለየ መልኩ የ13 ወር ፀጋና የመላው ጥቁር ህዝቦችና አፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት ሀገር ነን ብለዋል።
ብዝሃነቶቻችን የማንነታችን ጌጥና ድምቀት የአብሮነታችን ከፍታ እንጂ የልዩነቶቻችንንና የግጭት መንስኤ መሆን የለባቸውም ሲሉም ተናግረዋል።
ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሚደቀኑብንን ፈተናዎች በጋራ በመመከት የጀመርነውን ሀገራዊ የልማትና የብልፅግና ግስጋሴያችን በጋራ እውን ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ወ/ሮ መሰረት አመላክተዋል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማሪያም በበኩላቸው ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ማንነቶችንና እሴቶችን በመያዝ በአብሮነት ለዘመናት የዘለቀች ታላቅ ሀገር ናት ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህን ብዝሃነታችንና ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሚፈታተኑ ጉዳዮችን በምክክርና በውይይት በመፍታት አብሮነታችንን በማጠናከር የጀመርነውን ሀገራዊ የብልፅግና ጉዞ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል ብለዋል።
የመርሃግብሩ ተሳታፊዎች በሰጡን አስተያየት ኢትዮጵያዊነትና ህብረ ብሔራዊነት የማይነጣጠሉ እንደሆነ አውስተው፥ አንድነት፣ ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ካለ የማናሳካው ሀገራዊ ጉዳይ የለም ብለዋል።
እለቱን በማስመልከትም የማህበረሰብ አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የደም ልገሳ መርሃ ግብር የተካሄደ ሲሆን በመጨረሻም የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።
ዘጋቢ፡ ፍሰሀ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በዲላ ከተማ አስተዳደር ጳጉሜ 4 የህብር ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ በ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ አገልግሎት ለአቅመ ደካሞችና ድጋፍ ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ያስገነባቸውን የመኖሪያ ቤት ርክክብ አድርጓል
የ2019 ዘመን መለወጫና የመስቀል በአል በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የፀጥታ ሀይሉ በመቀናጀት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ