የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት በዞኑ ለሚከናወኑ ሥራዎች ከ10 ቢሊየን 7 መቶ 88 ሚሊየን 6 መቶ 12 ሺህ ብር በላይ በጀት አፀደቀ
ምክር ቤቱ በወልቂጤ ከተማ ሲያካሂድ የነበረው 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት 31ኛ መደበኛ ጉባኤውን አጠናቋል።
በምክር ቤቱ 4ኛ ዙር 13ኛ ዓመት 11ኛ መደበኛ ጉባኤ የዞኑ አስተዳደር ምክር ቤት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና ጠቋሚ ዕቅድን ጨምሮ ሌሎች የአፈፃፀም እና ጠቋሚ እቅዶች ቀርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በአባላቱ በሙሉ ድምፅ ፀድቀዋል።
በጉባኤው ክትትልና ድጋፍ በማጠናከር ፕሮጀክቶች በጥራት ተሠርተው ለማህበረሰቡ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የተናገሩት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ፤ ክፍተቶችን ለመሙላት ግብረ ሃይል ተዋቅሮ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የዞኑን ህዝብ የሰላም ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው የተቀናጀ ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ወልቂጤ ከተማን ለነሪዎቿ ምቹ ለማድረግ በርካታ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ እና ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥም አብራርተዋል።
በኢንቨስትመንት እና በስራ እድል ፈጠራ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በማጠናከር የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲጎለብት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አቶ ላጫ አስረድተዋል።
የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ኸይሩ መሐመድ በበኩላቸው፤ የህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተቋማቸው ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ተግባር በማከናውን ላይ እንደሚገኝና ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማመልከት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት በጉባኤው የቀረቡ ሪፖርቶችን መነሻ አድርገው በግብርና፣ በትምህርት በከተማ ልማት፣ በኢንቨስትመንትና በሌሎችም ዘርፎች በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች አንስተዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል።
ምክር ቤቱ በጉራጌ ዞን ለሚከናወኑ ሥራዎች የሚውል 10 ቢሊየን 7 መቶ 88 ሚሊየዮን 6 መቶ 12 ሺህ 5 መቶ ሰባት ብር በጀት ያፀደቀ ሲሆን ከ2018 በጀት አመት ሲነፃፀርም የ23 ነጥብ ስምንት በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ አቶ ረመዳን ጀማል የጉንችሬ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አድርጎ በመሾም ጉባኤውን አጠናቋል።
ዘጋቢ፡ ሪድዋን ሰፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ማሰራጨቱን አስታወቀ
የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ለሀገር እድገት ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ
በአሪ ዞን የባኮ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ