የመንገድ መሠረተ ልማት ሥራዎች ለሀገር እድገት ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በደቡብ ኦሞ ዞን የማሌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ
ለበርካታ ዓመታት ወረዳዉን ከዞን ማእከልና ቀበሌን ከቀበሌ የሚያገናኝ መንገድ እና የኮይቤ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጋር የሚያገናኝ መንገድ ችግርን መቅረፍ የሚያስችል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነዉ ነዋሪዎች የሚያነሱት፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡት የወረዳው ነዋሪዎች መከላከል አቶ ግዛዉ ግምጃ ለማ ሱሜ መልካሙ ቱራዣ እና ወይዘሮ ዘማነሽ ሥረጋ በጋራ እንደገለፁት፤ አሁን ላይ በልዩ ሁኔታ በሁሉም የወረዳው ክላስተሮች እየተካሄዱ የሚገኙ የመንገድና የድልድይ ስራዎች ለበርካታ አመታት ምላሽ ያላገኙ የህዝቡን ጥያቄዎች እየመለሰ የሚገኝ አስደሳች ተግባር ነው።
በ2018 ዓ.ም ግንቦት ወር በተካሄደው 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ በማሌ ወረዳ ተፎካካሪ ከነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በኢትዮጵያ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲን በመወከል የተወዳደሩት አቶ ብርሃኑ ዳሞ በበኩላቸው፤ የመንገዱ ስራ አሁን በሚታየዉ ልክ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ወደ ተግባር መገባቱ የህብረተሰቡ አንገብጋቢ የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች እየተመለሱ በመሆናቸዉ ደስታ የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የማሌ ወረዳ ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አማር ባርጩማ በበኩላቸዉ፤ የወረዳው ህዝብ ከሚያነሳቸው የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች መካከል የመንገድ መሠረተ ልማት ቀዳሚ እንደነበር እና በአሁኑ ሰዓት በአጭር ጊዜ ወደ 54 ኪሎ ሜትር የሚሆን የመንገድ ስራ በተለያዩ የመንገድ ሥራ በፌደራልና በክልል መንግሥት እንዲሁም በህብርተሰቡ ተሳትፎ በተፋጠነ መልኩ እየተከናወኑ እንደሆነ አብራርተዋል።
የተጀመረዉ የመንገድ ስራ ሲጠናቀቅ ህብርተሰቡ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል በወረዳው ማዕከል እና ኮይቤ ቀበሌ መናኸሪያ እያዘጋጀ እንደሚገኝ ሀላፊዉ አያይዘው አሰረድተዋል።
የማሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አልጋጋ ባልንሴ እንደገለፁት፤ ወረዳዉ ሰፋ ያለ የመንገድ ችግረ የነበረበትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየ መሆኑን ጠቁመዋል።
አያይዘዉም ወረዳዉ ለክልሉ ባቀረበዉ ጥያቄ መሠረት ክልሉም ፈጣን ምላሽ በመስጠት የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮጀክት RcAFs እንዲታቀፋ በማድረግ የመንገድ ተደራሽነትን በዘላቂነት ሊፈታ በሚችል መልኩ እየተሰራ እንደሚገኝ አስርድተዋል።
ዘጋቢ፡ ዳኛቸው ደሴ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማነታቸው የተረጋገጠ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ማሰራጨቱን አስታወቀ
የጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት በዞኑ ለሚከናወኑ ሥራዎች ከ10 ቢሊየን 7 መቶ 88 ሚሊየን 6 መቶ 12 ሺህ ብር በላይ በጀት አፀደቀ
በአሪ ዞን የባኮ ዳውላ ኣሪ ወረዳ ምክር ቤት ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን 4ኛ ዙር 14ኛ ዓመት የስራ ዘመን 18ኛ መደበኛ ጉባኤ ተጠናቀቀ