በወረዳው በእናቶች እና የህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፈ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

በወረዳው በእናቶች እና የህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፈ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

‎የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት በበኩሉ የእናቶችንና የህጻናትን ጤና ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንና ይህንንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

‎በጌዴኦ ዞን በይርጋጨፌ ወረዳ 7 ጤና አጠባበቅ ጣቢያዎች እና 26 የጤና ኬላዎች የሚገኙ ሲሆኑ፥ በዚህም ከ130 በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እና ከ180 በላይ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ለእናቶች እና ህጻናት ጭምር በወረዳው ለሚገኙ 230 ሺህ ህዝብ የጤና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

‎ወ/ሮ ሳራ ነጻነት እና መሠረት ብርሃኑ የወረዳው ነዋሪዎች ሲሆኑ የጤና ኤክስተንሽን ባለሙያዎች ቤት ለቤት እና በሴቶች የልማት ቡድን በማደራጀት በጤና ተቋማት መውለድ ያለውን ፋይዳ በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ባገኙት የግንዛቤ መነሻ ከቅድመ ወሊድ ጀምሮ እስከሚወልዱ ድርስ የጤና ክትትል አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎አሁን ላይ እናቶች ምጥ ሲይዛቸው ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ የአምቡላንስ አገልግሎት እንደሚሰጥ እና ይህም የእናቶችንና ጨቅላ ህጻናት ደህንነት ከመጠበቅ ባሻገር ለአባወራዎችም እፎይታ የሰጠ ጉዳይ መሆኑን ሌላኛው የወረዳው ነዋሪ አቶ ሀብታሙ ጥላሁን ተናግረዋል።

‎በተለይም ወላድ እናቶች የተሟላ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ የእናቶች ማቆያ መኖሩን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፥ በወረዳው የእናቶች እና የህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‎ወይዘሮ የኔነሽ ታደሰ እና ሲሰተር ከፋይወርቅ አሰፋ በወረዳው የሰዴ ቀበሌ የጤና ኤክስተንሽን ባለሙያ እና የቆንጋ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ አዋላጅ ነርስ አስተባባሪዎች ሲሆኑ÷ በእናቶች እና ህጻናት ደህንነት እና ሥርዓት ምግብ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

‎በ2018 በጀት ዓመት በወረዳው ለ2 ሺህ 312 እናቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ለመስጠት አቅደው 781 እናቶች በወረዳው በሚገኙ ጤና ተቋም ወልደው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውንና በቀጣይ በዘርፉ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸውን በይርጋጨፌ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የእናቶች እና ህጻናት ስርዓተ ምግብ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ፍቅሩ አሰፋ ተናግረዋል።

‎የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካልኝ ጥላሁን በበኩላቸው፥ የወላድ እናቶችን ጤና ለመጠበቅ ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት ከሚሠራው ሥራ ባሻገር በወረዳው በአራት አምቡላንስ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንና በእናቶች ማቆያ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎አክለው በወረዳው የእናቶችንና የህጻናትን ጤና ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንና ይህንንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጿል።

‎ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፈ ጣቢያችን