ለኤልኒኖ የማይበገር ግብርናን መገንባትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የእንስሳት ጤና ጥበቃ፣ የዝርያ ማሻሻልና የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገለጸ

ለኤልኒኖ የማይበገር ግብርናን መገንባትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የእንስሳት ጤና ጥበቃ፣ የዝርያ ማሻሻልና የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገለጸ

ለኤልኒኖ የማይበገር ግብርናን መገንባትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የእንስሳት ጤና ጥበቃ፣ የዝርያ ማሻሻልና የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

«ከኤልኒኖ ተጽዕኖ በፊት ክትባትን በማጠናከር የእንስሳት ጤናን እንጠብቅ» በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የ2018/19 በጀት ዓመት የክትባት ዘመቻ ክልላዊ ማስጀመሪያ መርሃግብር በጋሞ ዞን ዳራማሎ ወረዳ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የዋጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አልማዝ አባይነህ ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት፣ የዝናብ እጥረቱን ተከትሎ በሰብል ላይ የደረሰው አደጋ በእንስሳት ላይ እንዳይደገም በሽታን የመከላከልና የመኖ እጥረትን የማቃለል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፥ ለዚሁ ስኬት ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምሴ አድማሱ (ዶ.ር) በበኩላቸው የክትባት ዘመቻው የተጠበቀውን ውጤት ያመጣ ዘንድ መርሃግብሩን በቅንጅት መምራትና ማስፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪ እና ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ.ር) እንደገለጹት፣ ዘመቻው ኤልኒኖ የማይበገር ግብርናን በመገንባት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።

አክለውም እንስሳት ለአርሶና አርብቶ አደሩ የችግር መፍቻ የኢኮኖሚ ምንጭና ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመሆኑም የእንስሳትን ጤና በመጠበቅ፣ የዝሪያ ማሻሻልና የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ : አማሮ አርሳባ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን