በበጎ ተግባራት ላይ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት ድርሻ የጎላ መሆኑ ተገለጸ
የባስኬቶ ዞን ልማት ማህበር በክረምት በጎ ተግባር ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካማና አረጋዊያን ቤት ግንባታ አስጀምሯል።
በክረምት ወራት በሚከናወኑ ከ18 በላይ ዘርፎች በርካታ አቅመ ደካማ ወገኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
የባስኬቶ ዞን ልማት ማህበር ጧሪ ለሌላቸው ወገኖች የሚያሠራው የመኖሪያ ቤት ግንባታ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የባስኬቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር በዛብህ ገበዬሁ፥ በክረምት ወራት የዞኑን ባለሀብቶች፣ የሲቪክ ተቋማትን በማስተባበር እንዲሁም በዞኑ መንግስት በአዲስ መልክ በተሠሩ 24 የቤት ግንባታዎች ከ200 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል።
በግብርና፣ በጤናና ትምህርት እንዲሁም በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት ከመንግስትና ከህዝብ ሊወጣ የነበረን ከፍተኛ ሀብት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል።
በበጎ ተግባራት ላይ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሲቪክ ማህበራት ያላቸው ድርሻ የጎላ መሆኑን አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።
በክረምቱ የተጀመረው የበጎ ተግባር ሥራ የመንግስት ሰው ተኮር ፖሊሲ ማሳያ መሆኑን ያነሱት አስተዳዳሪው፥ በቀጣይም ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማስተባበር በበጋው ወራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የባስኬቶ ዞን ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ሴልቆ ልማት ማህበሩ የመንግስተን የልማት ክፍተት ህብረተሰቡን በማሳተፍ እንዲሟላ ሲያደርግ መቆየቱን አብራርተዋል።
በልማት ስራው ጎን ለጎን በሰብአዊ ድጋፎችና በክረምት በጎ ሥራዎች በመሣተፍ በየግዜው የአረጋዊያንን ቤት መጠገንና በአዲስ መልክ የመሥራት ተግባር ላይ የነቃ ተሳትፎ ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።
በቤት ግንባታ ሂደቱ ላይ ያነጋገርናቸው የአካባቢው ባለሀብት አቶ ሰይድ ጉዳዶ የልማት ማህበሩን በገንዘብ ከመደገፍ ባለፈ የከተማውን ባለሐብቶች በማስተባበር ለበርካታ አቅመ ደካማ አረጋዊያን የቤት ግንባታ ማከናወን መቻሉን አንስተዋል።
በዕለቱ የቤት ግንባታ የተጀመረላቸው አረጋዊ ለተደረገላቸው ድጋፍ ከልብ አመሥግነው ከቅርብ ግዜ ወዲህ መንግስት ለአቅመ ደካማ አረጋዊያን የሰጠው ትኩረት እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ: አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በወረዳው በእናቶች እና የህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፈ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ
በዞኑ የቱሪስት ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የኮንሶ ዞን ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ
ለኤልኒኖ የማይበገር ግብርናን መገንባትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የእንስሳት ጤና ጥበቃ፣ የዝርያ ማሻሻልና የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተገለጸ