የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በማጠናከር ክልላዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ

የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በማጠናከር ክልላዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2018 የፓርቲ ስራዎች የማጠቃለያ ግምገማና የ2019 ዕቅድ ኦሬንቴሽን መድረክ በሳዉላ ከተማ ተካሂዷል።

መድረኩን የመሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በማጠናከር ክልላዊ አንድነትን ማጎልበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአመራር የስነ-ምግባር ልህቀት ማረጋገጥ አለመቻል፣ የፓርቲውን አቅም አሟጦ አለመጠቀም እንዲሁም ነጠላ ትርክቶችን በሚፈለገው ደረጃ ማምከን አለመቻል በበጀት ዓመቱ የተስተዋሉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አቶ ገ/መስቀል አንስተዋል።።

በአዲሱ የበጀት ዓመት የአመራርና አባላት ጥራትን ማረጋገጥ፣ ብሔራዊ ገዢ ትርክትን ማስረፅ እና የፓርቲውን ተቋማዊ ስራዎች በግልፅ በሚቀመጡ ደረጃዎች ማረጋገጥ ትኩረት የሚደረግባቸው መሆናቸዉን አስረድተዋል።

በተለይም ክልላዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ አስተሳሳሪ ትርክቶች መገንባት ላይ በከፍተኛ ትኩረት በመስራት የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ማጠናከር እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

በክልሉ ብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማሩፋ መኩሪያ፤ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በክልሉ በተከናወኑ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዘርፍ ተግባራት አመርቂ ዉጤት የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

በ2018 ዓ.ም የምርጫና መደበኛ የልማት ስራዎች በተቀናጀ መንገድ በተሰራው ስራ የተሻለ ዉጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ጠንካራ ፓርቲ ለጠንካራ መንግስትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ማሩፋ፤ በ2019 የበጀት ዓመት የፓርቲውን ተቋማዊ አቅም ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

“በ2019 የበጀት ዓመት የፓርቲውን አቅም በተሟላ መንገድ በመጠቀም የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ከመድረኩ የተሻለ ተሞክሮና ልምድ የተወሰደበት መሆኑን ጠቅሰው ለተግባራዊነቱም እንደሚረባረቡ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን