ምክር ቤቱ 2ኛ ዙር 31ኛ መደበኛ ጉባኤ አካሂዷል።
በጉባኤው የ2018 በጀት ዓመት የ3ኛ ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የይርጋጨፌ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታዬ ታደሰ በከተማው ህዝብ የሚያነሳቸውን የልማት፣ የዕድገት፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትሐዊ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥያቄዎችን ለመመለስ የምክር ቤቱ አባላት በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት።
አፈ ጉባኤው አያይዘውም የከተማ ግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ በሁሉም አካባቢዎች በተሠሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አስገንዝበዋል።
በየደረጃው ያሉ አመራር አካላት ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ በባለቤትነት ስሜት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ የከተማ አስተዳደሩን አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሁሉም የልማት ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዋል።
በቀጣይም ለከተማው ሁለንተናዊ ዕድገት በማፋጠን ቀጣይነት ያለውን የሕዝቡን የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በመንግሥት የተጀመሩትን ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመብራት ኃይል መቆራረጥ፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በመድኃኒት እጥረት፣ በአንዳንድ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁስ እጥረት በዘርፉ እንደ ችግሮች የተገመገሙ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው መዋቅሮች ጋር እየተመካከሩ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት በከተማ ልማት ተጨባጭ ለውጥ ቢመዘገብም በጤና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በመብራት ሃይል መቆራረጥ፣ በትምህርት ጥራትና በሌሎች ዘርፎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል።
ዘጋቢ: ውብሸት ኃይለማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ሙስሊሙ የመውሊድ በዓልን ሲያከብር በብዝሃነት ውስጥ የሚንፀባረቁ የመረዳዳትና የአብሮነት በጎ እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የየዞን ከፍተኛ አመራሮች በሣውላ ማረሚያ ተቋም አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ጎበኙ
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ልየታ ተካሄደ