በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ ከ154 ሚሊዮን በላይ ዘርፈብዙ ጥቅም ያለቸውን የተለያዩ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ ከ154 ሚሊዮን በላይ ዘርፈብዙ ጥቅም ያለቸውን የተለያዩ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ከ154 ሚሊዮን በላይ ዘርፈብዙ ጥቅም ያለቸውን የተለያዩ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱን የሀድያ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ዞናዊ የችግኝ ተከለ መርሀ-ግብር ”ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል በሆሳዕና ከተማ ቢር ዋቸሞ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ቅጥር ጊቢ ተካሂዷል።

በመርሀ-ግብሩ የተሳተፉት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ(ዶ/ር) ኢንሼቲቭ የሆነው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ከተጀመረ ወዲህ ተስማሚ የአከባቢ አየር ንብረት እየተፈጠረ ከመምጣቱም ባለፈ፥ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አንጻር የማይተካ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

ከዚህ መነሻም በዘንድሮ መርሀ-ግብር ከ150 ሚሊዮን በላይ ዘርፈብዙ ጥቅም የሚሰጡ የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል በማቀድ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፥ ዕቅዱ ግብ እንዲመታ ከባለድርሻ አካላት ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

የሀድያ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ሀብታሙ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ መርሀ-ግብሩ ከተጀመረ ወዲህ የተተከሉ ችግኞች ከንክኪ በጸዳ መልኩ በእንክብካቤ እንዲያድጉ ከመደረጉ የተነሣ ለሕብረተሰቡ ዘረፈ ብዙ ጥቅም መስጠት መጀመራቸውን አስረድተዋል።

የችግኞቹ ዞናዊ የጽድቀት መጠን 81 በመቶ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው በዘንድሮ መርሀግብር ለመትከል ከታቀደው ከ49ሺህ ሄክታር ውስጥ 29 ሺህ ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሀድያ ዞን ደንና አካባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰላሙ ደመቀ በበኩላቸው የዘንድሮ ችግኝ ተከለ ፕሮግራም ትምህርት ቤቶችና የሃይማኖት ተቋማትን በልዩ ሁኔታ ያካተተ እንደሆነ አንስተው ባለድርሻ አካላት ዕቅዱ እንዲሳካ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በመርሀ-ግብሩ የዞኑና የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን