የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ የሚገድቡ እንቅፋቶችን በትብብር መፍታት እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድናስር ገለጹ
በፈጠራ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣት ሴቶች እና የሥርዓተ ጾታ አካታችነት በተመለከተ ላለፉት ሦስት ዓመታት በሰባት የአፍሪካ ሀገራት ሲደረግ የቆየው የኢትዮጵያ ጥናት በተመለከተ በወልቂጤ ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሀመድናስር በዚሁ ወቅት፤ ሴቶች በተሳተፉባቸው መስኮች ሁሉ ተጨባጭ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ተናግረው ተሳትፎአቸውን የሚገድቡ እንቅፋቶችን በትብብር መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በሕግ የተቀመጡ ጉዳዮች ተፈጻሚነት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ማረም እንዲሁም መሻሻልና መካተት የሚገባቸው ጉዳዮች ላይም ትኩረት ያስፈልጋል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ፤ የጉራጌ ዞን በፈጠራ ስራ የተሰማሩና ለሌሎች ምሳሌ የሆኑ የፈጠራ ባለቤቶች የሚገኙበት መሆኑን ጠቁመዋል።
በኪነ ጥበብና በእደ ጥበብ የፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም በጎ ተጽእኖ እየፈጠሩ ስለመሆናቸው ጠቅሰው ባህላዊ የምህንድስና ጥበብ የሆነው የጉራጌ ጀፎረም የማህበረሰቡ ነባር የፈጠራ ጥበብ ማሳያ ነውም ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጥናት መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የጥናት ፕሮጀክቱ መሪ ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ እንዳሉት፤ ጥናቱ አዲስ አበባን ማዕከል በማድረግ በአዳማ፣ ሀዋሳ እና በወልቂጤ የሚገኙ ወጣት የፈጠራ ባለሙያ ሴቶች በዘርፉ ያሏቸው እድሎችና የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶችን ሲመረምር ቆይቷል።
በዚህም በስራ ቦታ የሚደርስ ጾታን መሰረት ያደረገ አድልዎና የተገደቡ እድሎች፣ ማህበራዊና ባህላዊ ጫናዎች ሴቶች ወደ ፈጠራው ዘርፍ እንዳይገቡና ውጤታማ ሆነው እንዳይቀጥሉ የሚያደርጉ እንቅፋቶች መሆናቸው በጥናቱ ተለይቷል ብለዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር የሺሀረግ አፈራ፤ ሴቶች የባለብዙ ተሰጥኦ ባለቤቶች ቢሆኑም እኩል የስራና የትምህርት እድል አለማግኘታቸው ወደፊት እንዳይወጡ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።
በመሆኑም ጥናቱ ያመላከታቸውን ችግሮች ለመቅረፍና ተሳትፎአቸውን ለማሳደግ በትብብር መስራት እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።
በውይይቱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ፣ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ተመራማሪዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ የግብርና ስራዎችን ተመለከተ
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለውጥ የሚበጅ፤ ዘመኑን በሚዋጅ የቴክኖሎጂ እውቀት የበለጸጉ ዜጎች የሚፈልቁበት ተቋም ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ39ኛ ዙር የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በደመቀ ሁኔታ እያካሄደ ይገኛል