ግምቱ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃ በኅብረተሰቡ ጥቆማ መያዙን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ግምቱ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃ በኅብረተሰቡ ጥቆማ መያዙን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አስታውቋል።
ኅብረተሰቡ ህገወጦችንና ህገወጥ ተግባርን ለመከላከላል በሚደረገው ጥረት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል።
በወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የፖሊስ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ማስተባበሪያ ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር መብራቱ ቂልጡ ህዝብንና መንግሥስትን የሚጎዱ የማጭበርበር ተግባራት ላይ የተሰማሩ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ማህበረሰቡን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም የአሁኑን ጨምሮ ቅርብ ጊዜ በኅብረተሰብ ጥቆማ የተያዙ የኮንትሮባንድ ዕቀዎች ማሳያ መሆናቸውን ኃላፊው አክለዋል።
በጽ/ቤቱ የሥነ ምግባርና መከታተያ ክፍል ኦፊሰር ረዳት ኢንስፔክተር ያቆብ ሽፈራው ፖሊሶች በሥነ ምግባር ታንፀው ለሌሎች አርአያ በመሆን የተቋሙን ተልዕኮ በታማኝነት እንዲወጡ መጠነ ሰፊ ሥራ ከመሥራትም ባሻገር ወንጀልና አደጋን ከመከላከል ረገድ በቅንጅት በመሠራቱ ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑን ገልፀዋል።
ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት ምትኩ የይርጋጨፌ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ናቸው። መነሻውን ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ቀርጫ ከተማ በማድረግ በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳን አቋርጦ ወደ መሀል አገር ለማለፍ የሞከረው ኮንትሮባንድ ዕቃ የጫነው ታሽከርካሪ በወረዳው ቆንጋ ቀበሌ መያዙን ተናግረዋል።
በኅብረተሰቡ ጥቆማ ፖሊሶች ባደረጉት ብርቱ ክትትል ግምታቸው ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዛቸውን የገለጹት ረዳት ኢንስፔክተር ታምራት ከዕቀዎቹም አልባሳትና ቅሽር ቡና እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
የመኪናው አሽከርካሪ ተግባሩን ህጋዊ ለማስመሰል ከላይ ቡና ከውስጥ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ደብቆ በመጫን ህጋዊ ወረቀት ይዞ በማሳየት ከውስን ፍተሻ ጣቢያዎች አልፎ ለመሄድ እየጣረ ባለበት ቁጥጥር ሥር መዋሉንም ረዳት ኢንስፔክቴር ታምራት አስረድተዋል።
የመንግስትን የኢኮኖሚ አቅም በሚያዳክሙ ህገ ወጥ ተግባራት ተሰማርተው ለግል ጥቅማቸው የሚሠሩ ህገወጦችንና የወንጀል ተግባራቸውን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡ ላደረገው ጥቆማና ትብብር አዛዡ አመስግነው በቀጣይም ሁሉም በባለቤትነት ስሜት ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፡ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባስጀመረው የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ፕሮግራም ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ
የይርጋጨፌ ከተማን የኮሪዴር ልማት ለነዋሪዎች ምቹ ከተማ እንዲትሆን ከማድረግ ባለፈ የከተማዋን ገፅታ የቀየረ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ
የፍትህ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ በዘርፉ እየታዩ ያሉ ማነቆዎችን ማረም እንደሚገባ ተገለፀ