ሀገራዊ የምክክር ኮምሽኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች አካታች መሆኑ በህዝብ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታ እምነታቸው መሆኑን በቤንች ሸኮ ዞን በምክክር ኮሚሽኑ ውይይት ላይ የተሳተፉ ተሳታፊዎች ተናገሩ

ሀገራዊ የምክክር ኮምሽኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች አካታች መሆኑ በህዝብ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታ እምነታቸው መሆኑን በቤንች ሸኮ ዞን በምክክር ኮሚሽኑ ውይይት ላይ የተሳተፉ ተሳታፊዎች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 16/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሀገራዊ የምክክር ኮምሽኑ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች አካታች መሆኑ በህዝብ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንደሚፈታ እምነታቸው መሆኑን በቤንች ሸኮ ዞን በምክክር ኮሚሽኑ ውይይት ላይ የተሳተፉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

በዞኑ በሁለት ዙር 3 ሺ 6 መቶ ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውም ተጠቁሟል።

እየተስተዋሉ ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት ያስችል ዘንድ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ 1265/2014 ተቋቁሞ ወደስራ ተገብቷል። ኮሚሽኑ የሶስት አመት የቆይታ ጊዜ እንዳለው እና በአሁኑ ሰአትም የዝግጅት ምእራፉን ጨርሶ ወደተግባር ገብቷል።

ኮሚሽኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚወከሉ ሁለት ሁለት የህዝብ ወኪሎችን እያስመረጠ ይገኛል።

በውይይቱ ከተሳተፉት ተሳታፊዎች ውስጥ አንዱ የሆኑት እና በንግዱ ዘርፍ የተወከሉ አቶ አንተነህ አዲሱ እንደተናገሩት ሀገራዊ የምክክር መድረኩ መዘጋጀቱ ልዩነቶችን በመግባባት ከመፍታት ባሻገርም የነጋዴው ማህበረሰብ የሚያነሳውን ጥያቄ በተገቢው ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ ያስችላል።

የመንግስት ሰራተኛ እና መምህራንን ወክለው የተገኙት ወይዘሮ ልኬለሽ መኮንን እና መምህር ገበየሁ ጎዱ በአሁኑ ሰአት በሰራተኛው ይሁን በመምህራን የሚነሱ በርካታ ያልተመለሱ እና ከሚመለከተው አካል ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች መኖራቸውን ተናግረው የዚህ ሀገራዊ ምክክር መድረክ በሀገር ደረጃ መዘጋጀቱ ጥያቄያቸውን በተገቢው ለሚመለከተው አካል በማቅረብ የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ እድል እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።

አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው ከሀገራዊ ምክክር መድረኩ እንዳይሳተፉ እንዳላደረጋቸው እና በውይይቱ መሳተፋቸው በሀገራዊ ጉዳይ እኩል ድርሻ እንዳላቸው ያመላከተ መሆኑን እና ምክክር ጉባኤው ላይ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ጌታቸው ባይከዳ ናቸው።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውክልና እና ወገንተኝነት ነጻ የሆነ እና በህዝብ ውክልና ድምጽ የተመረጡ አባላትን ይዞ የተቋቋመ ኮሚሽን መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰአትም ህዝቡ የሚያነሳውን የጥያቄ አጀንዳ ለመቅረጽ እየተሰራ ሲሆን በሲዳማ፣ በጋምቤላ አሁን ደግሞ በደቡብ ምእራብ ክልሎች የህዝብ ወኪሎችን በማስመረጥ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህዝቡ የሚያነሳውን አጀንዳ በፖሊሲ ተቀርጾ ለፓርላማ ለአስፈጻሚ ተቋም እንዲሁም ለመንግስት ይቀርባልም ብለዋል።

በቤንች ሸኮ ዞን በተደረገው ውይይትም ከዞኑ ስድስት ወረዳዎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ1 ሺ 6 መቶ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ በክልል የሚሳተፉ ሁለት ሁለት ተወካዮቻቸውን መምረጣቸውን ጠቁመዋል።

ለውይይቱ ስኬትም የተባበሩ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲንም ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን