18ኛዉ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በቦንጋ ከተማ ተከበረ
ሀዋሳ፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሰንደቅ ዓላማችን የአንድነታችንና የድል ምልክታችን በመሆኑ ክብሩን ጠብቆ በትዉልድ እንዲዘከር ማድረግ ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ተናገሩ፡፡
18ኛዉ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በቦንጋ ከተማ የክልልና የዞን እንዲሁም የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
በአከባበር ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባንዲራ አባቶቻችን ታግለዉ የሀገራቸዉን ሉዓላዊነት ያስጠበቁበት የድል አርማ ነዉ ብለዋል፡፡
እንደ ሰንደቅ ዓላማ የጋራ ትርክትን የሚገነባው የአድዋ ድል በሁሉም ኢትዮጵያዊያን አስተዋጽኦ ተገንብቶ የተመረቀዉ የታላቁ ህዳሴ ግድብንም ለአብነት አንስተዋል፡፡
ጥቃቅን ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ መሆናችንን የምናሳይበት ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የአከባበር ስነ-ስርዓቱን ማጠናከርና ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የካፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ግርማ ደፋር በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ሰንደቅ ዓላማችን ጥቅምት በገባ በመጀመሪያ ወር እንዲከበር በአዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ ከሆነ 18ኛ ዓመት ማስቆጠሩን ገልጸዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ክብር ለማሰቀጠል ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነዉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፋና ወጊ ድል ለአፍሪካዊያን አሳይታለች ያሉት አቶ ግርማ ይህም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በትዉልድ ግንባታ ላይ ለመስራት ሁሉም ዝግጁ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የሰንደቅ ዓላማ አከባበርን በተመለከተ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሴ ወልደ ጊዮርጊስ ሰነድ አቅርበዉ ዉይይት ተደርጓል፡፡
የጋራ እሴቶችን ማጠናከርና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን መገንባት የበዓሉ ዓላማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የዘንድሮዉ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የመከበሩ ምስጢር ዜጎች የሰንደቅ ዓላማ ምንነት እንዲረዱና በገቡበት የስራ መስካቸዉ ሀገራዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ ተግባር እንዲፈጽሙ ለማስቻል ነዉ ብለዋል፡፡
አዘጋጅ፡ በአካሉ ወልደ ኢየሱስ – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም #ደሬቴድ – ቀጥታ ስርጭት
በኮሬ ዞን ምክር ቤት 18ኛው የሰንደቅዓላማ ቀን በደማቅ ሁኔታ ተከበረ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 02/2018 ዓ.ም