ጊዜው ደርሶ እንደዚህ ሆነ
በጌቱ ሻንቆ
ዜን ጃፓንኛ ነው። አስተምህሮው ጃፓን ቢወለድም የተወለደችበት ግን ቻይና ናት። እንደመንፈስ ተሀድሶ ነው። ዛሬን ከትላንት የተሻለ ለማድረግ ሞራላዊ ጥያቄዎችን እያነሳ ምላሽ ፍለጋ ይዞራል። በዚህ የመንፈስ ተሀድሶ የሞራል ልዕልና መንገድ አልፈው ቻይናን ያሳለፏት በርካታ መምህራን ነበሯት።
ከነዚህ መምህራን መካከል ጥቂቶቹ ዛሬ ለምን ከኛ ጋር አይሆኑም?
ጉዶ የሚባለው የዜን መምህር በቻይና ምድር ላይ ከፍ ያለ ነበር- እንደ ሠንደቅ አላማ ነበር ከፍታው። በአንድ ወቅት ወደዚህ መምህር ንጉስ የሆነ ሠው መጣ።
ንጉሱ ጉዶን ፦
” የአንድ ሠው እውቀት ከሞት በዃላ ምን ይሆናል? ” ፣ ብሎ ጠየቀው።
” እኔ ይህንን አውቅ ዘንድ እንዴት እችላለሁ?”፣ ብሎ ጥያቄውን በጥያቄ መለሠ።
“ምክንያቱም አንተ ጠቢብ ስለሆንክ”፣ አለው።
” ልክ ነህ። እኔ ግን ያልሞትኩት ነኝ” ፣ ብሎ የንጉሱን ጥያቄ ዘጋው።
ዜን እኔነትን የመፈለግ ጥበብም ነው። አንድ ጆሹ የተባለ ሠው ነበር። ይህ ሠው እኔነትን የመፈለግ ትምህርት መቅሰም የጀመረው ዕድሜው ስልሳ ከረገጠ በዃላ ነበረ። ጆሹ ከስልሳ ዓመት እድሜው በዃላ ያለማቋረጥ እራሱን ሲያነቃ፣ ጥበቡን ሲማር፣ ጉድለቱን ሲሞላ ኖረ። ሰማንያ ዓመት ከሞላው ወዲህና የዕድሜው ቆጣሪ መቶ ሀያ እስኪደርስ ጥበብን እያስተማረ ነው የዘለቀው።
በመምህርነት ዘመኑ አንድ ጊዜ ከተማሪዎቹ አንዱ እንዲህ ሲል ጠየቀው፦
“መምህር አንጎሌ ባዶ ነው። እንደው ምናባቴ ባደርግ ይሻለኛል?”
ጆሹ፦
“ምንም ነገር የሌለው ከሆነማ ምን ታደርጋለህ! ከጭንቅላትህ ውስጥ አንጎልህን አውልቀህ ወርውረው”
ተማሪው፦
“ምንም ነገር የሌለው ነው አልኩህኮ። ምንም ነገር የሌለው ከሆነ አውጥቼ የምወረውረውን ከየት አመጣለሁ?”
“በጣም ጥሩ። ባዶውን ቅል ተሸክመህ ዙራ”፣ አለው -ጆሹ።
በንኬስ የሚባል ሌላም የዜን መምህር ነበር። የባንኬስ ንግግሮች የመንፈስ ምላስ ጥርግ አድርጎ የሚልሳቸው፣ አንደ ወለላ ማር ጥፍጥ ያሉ ነበሩ። የባንኬስን ንግግሮች ለማድመጥ የሚሰበሰቡት የዜን ተማሪዎች ብቻ አልነበሩም። በሁሉም የኑሮ ደረጃዎች የሚገኙ ሌሎች ሠዎችም ንግግሮቹን ለማዳመጥ ዙሪያውን ይከቡ ነበር።
በንኬስ ንግግሮቹን በመስማት ጉጉት ተስበው ለመጡት ተከታዮቹ ዲስኩር ሢያንቆረቁር የሚጠቅሳቸው ቅዱሳት መፃህፍት የሉም። የንግግሮቹ ሁሉ ምንጭ አንጎሉ ነበር።
አንድ ጊዜ በርካታ ተከታዮች ያሉት መሆኑ ያበሳጨው፣ ቅናት በልቡ የተዘራበት ሠው ባንኬስን ባደባባይ የማሳፈር ቂሪላ ሀሳብ ተጭኖ መጣ። የተለመደ ንግግሩን እያሰማ ሳለ አቋረጠውና “ሠላም ላንተ ይሁን መምህር!…”፣ ብሎ ጀመረ። “ሠላም ላንተ ይሁን መምህር! ይቅርታ አንድ ጊዜ! አንተን ብዙ ሠዎች ያከብሩሀል። አንተን ያከበረ ሁሉ ደግሞ ላንተ መታዘዝ ይኖርበታል። እንደኔ ያለ ሠው ግን ላንተ የሚሰጠው ክብር የለም። እስኪ አሁን እኔን ላንተ የምታዘዝ ሠው አድርገህ ማሳየት ትችላለህ?”፣ አለው።
ባንኬስ ፦
” አዎን። እንዳሳይህ ናና በጀርባዬ በኩል ቁም!”፣ አለው።
ሠውየው የተሠበሠበውን ሠው እየሰነጠቀ መጥቶ ከባንኬስ በስተጀርባ ቆመ። ባንኬስ እንደገና ፦
” አልተመቸኝም። በስተቀኜ ሁን!”፣ አለው።
በበስተቀኙ አቅጣጫ መጣ።
አሁንም ባንኬስ ፦
” ይበልጥ የሚመቸኝ ግን በስተግራዬ ብትሆን ነው”፣ አለው።
ሰውየው በበስተግራው በኩል መጣ። ሰውየው ባንኬስ ያዘዘውን ሁሉ ተቀብሎ ፈፀመ።
በመጨረሻም ባንኬስ፦
“ታዛዤ ነህ። በል አሁን ተቀመጥና የምለውን አዳምጥ”፣ አለው።
ሴንጋይ ተብሎ የሚጠራ አንድ የዜን ጠቢብ ነበር። አንድ ባለፀጋ የሆነ ሠው ባለፀጋነቱ ምንም ሳይቋረጥ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገርበትን ጥበብ ይገልፅለት ዘንድ ሴንጋይን ጠየቀው።
ሴንጋይ ወረቀት ሳበና ተከታዩን ፃፈ፦
“አባት ይሞታል። ልጅም ይሞታል። የልጅ ልጅም ይሞታል “
ባለፀጋው ሰው የተፃፈውን ነገር ተመለከተና በእጅጉ ተበሳጨ። በንዴትና በሀይለ ቃል፣” እኔ ቤተሰቤን ደስ የሚያሠኝ ነገር ፅፈህ ስጠኝ እያልኩህ አንተ ግን ታፌዝብኛለህ!?”
“እያፌዝኩ አይደለም። ከልጅህ ቀድመህ አንተ ብትሞት፣ ልጅህም ካንተ በኻላ ቢሞት። የልጅ ልጅህም ልጅህን ተከትሎ ቢሞት። ነገር ግን አንተ በህይወት ቆመህ፣ ልጅህም ሳያልፍ የልጅ ልጅህ በሞት ቢለይ የቤተሰቡ ልብ ይሰበራል። ትውልድ ትውልድን ተከትሎ ቢያልፍ የተፈጥሮን መስመር ተከትሎ ነው። እኔ እንዲህ ያለውን ማለፍ ነው ፀጋ የምለው”
አካክዩን የተባለው ሰው ብልህነትን ገንዘቡ ያደረገ የዜን ጥበበኛ ነበረ። አንድ ጊዜ የመምህሩ ውድ የሻይ ሲኒ ተሠበረበትና በጣም ተጨነቀ። ለመምህሩ ስለተሠበረው ሲኒ “ምን ብዬ ነው የምነግረው?”፣ እያለ ሲጨነቅ የመምህሩ መምጣት ኮቴ ተሠማ።
አካክዪን በፍጥነት የሲኒውን ስባሪዎች ደበቀ።
መምህሩ ወደ ቤት ገባ። ገብቶ ጥቂት እረፍት እንደወሰደ፣” ለምንድነው ነገሮች የሚሞቱት?” አለው።
“አንድ ነገር የተፈጠረው ነገሮች ተሰባስበው እንደሆነ ሁሉ፣ የተሠባሠቡት ነገሮች መልሰው ይለያዩ ዘንድ የተፈጥሮ ግዴታ ስለሆነ ነው። ሞት የተፈጥሮ ግዴታ ነው። ጊዜው ሲደርስ ሁሉም ነገር በዚህ መንገድ ይሸኛል”፣ አለው።
አካክዩንም፦
“መምህር ሆይ! ያንተም ሲኒ ጊዜው ደርሶ እንደዚህ ሆነ”፣ አለና ስብርባሪዎቹን አሳየው።
“የሠው ዓመል ዘጠኝ፣ አንዱን ለኔ ስጠኝ”
More Stories
በከተሞች የሚስተዋሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ሰፊ ድርሻ እንዳለው ተገለጸ
ማህበራዊ ሚዲያን በአግባቡ በመምራት እና በመጠቀም የአካባቢን ገጽታ መገንባት እንደሚገባ ተጠቆመ
የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መስፋፋት ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተገለጸ