በመሐሪ አድነው
የዛሬው የንጋት እንግዳችን ወ/ሮ ወይንሸት መንገሻ ይባላሉ፡፡ የሲዳማ ልማት ማህበር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ናቸው፡፡ ትውልድና እድገታቸውን፤ የልማት ማህበሩን የስራ እንቅስቃሴና ተያያዥ ጉዳዮችን እያወጋን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ
ንጋት፡– በቅድሚያ ለቃለ መጠይቁ ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
ወ/ሮ ወይንሸት፡– እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡– ወ/ሮ ወይንሸት ማን ናቸው ትውልድና እድገትዎን ይንገሩን?
ወ/ሮ ወይንሸት፡– ተወልጄ የደኩት በሲዳማ ክልል፥ ሀገረ ሰላም ወረዳ፥ ጋሴ ቀበሌ ነው፡፡ ልጅነቴን በገጠር ነው የኖርኩት። የገጠሩንም የከተማውንም አኗኗር አይቼ ማደግ በመቻሌ እድለኛ ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
ለቤተሰቤ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ አባቴ መምህር ነበር፡፡ ልጆቿን ከምትወድ እናት ነው የተወለድኩት፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በጋሴ ቀበሌ ሃላቃ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡ በመቀጠል ለከተማ ቅርብ ወደ ሆነው መካነ ኢየሱስ ት/ቤት ገብቼ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተማርኩኝ። አባቴ ከመምህርነት ወደ ትምህርት ጽ/ቤት ሲገባ እኔም ተከትዬው ደጃዝማች ባልቻ ት/ቤት ተመዘገብኩኝ፡፡
በትምህርት አቀባበል መካከለኛ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ ነበርኩኝ፡፡ የት/ቤቱ ርእሰ መምህር ከአባቴ ጋር ይቀራረቡ ስለነበር እኔን ባየኝ ቁጥር “ይህች ልጅ ጎበዝ ተማሪ ናት” ይል ነበር፡፡ ሃሳቡን ደጋግሜ ስሰማ የልጅነት አእምሮዬ አመነ፡፡ እኔም ከዚያ ጀምሮ ውጤቴን በማሻሻል በደረጃ ማለፍ ጀመርኩኝ፡፡
በከፍተኛ ውጤት ከክፍል ክፍል እዘዋወር ነበር፡፡ በቀለም ትምህርት ውድድር የመለስተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ጋር ተወዳድሬ በማሸነፍ የባልቻን ት/ቤት ማስጠራቴን አስታውሳለሁ። ሴትም ሆኜ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በማሸነፌ ት/ቤቱ ትልቅ አድናቆትና ሽልማትም አበርክቶልኛል፡፡
ብቃቴን ያዩት ቤተሰቦቼ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በሀዋሳ እንድማር ተስማምተው ላኩኝ፡፡ ጥሩ ትምህርት መማር አለባት በሚል ወደ ኮምቦኒ ገባሁ፡፡ እዚያ ደግሞ ለመመዝገብ ውድድር ያስፈልግ ነበር፡፡ ተወዳድሬም አለፍኩኝ፡፡ ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ በኮምቦኒ መማር ጀመርኩኝ፡፡
በዚህ አጋጣሚ ማንሳት የምፈልገው አእምሮህ ነፃ ካልሆነ በትምህርት ውጤታማ መሆን አይቻልም፡፡ እኔ ከሀገረ ሰላም መጥቼ ሀዋሳ ኮምቦኒ ት/ቤት ስገባ በጣም ልጅ ስለነበርኩኝ ዘመድ ጋር ሆኜ እንድማር ነበር ቤተሰቦቼ የፈለጉት፡፡ እኔም ከቤተሰብ ተለይቼ መማር ስጀምር የመጀመሪያዬ ስለሆነ ከአዲስ ቤተሰብ ጋር መዋሀድ በጣም ተቸገርኩኝ፡፡ ስምምነትም ጠፋ፡፡ ሁኔታውን ለቤተሰብ ለመግለጽም እነርሱ እንዳይጨነቁ በማሰብ አልተናገርኩኝም ነበር፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታው ለእኔ ጥሩ አልነበረም፡፡ ይህ ችግር ደግሞ በትምህርቴ ተገለጸ፡፡ ከብዙ ልጆች ጋር ተወዳድሬ አልፌ የገባሁ ልጅ፥ ከክፍል ክፍል መዛወር አቅቶኝ ደገምኩ ማለት ነው። ጉዳዩን ቤተሰብም ተረዳና በቀጣዩ አመት ታናሽ እህቴ እንድትመጣ ተደርጎ ከእርሷ ጋር መኖር ጀመርን፡፡ አእምሮዬ ሲረጋጋ ወደ ቀደመ ብቃቴ ተመልሼ በደረጃ የአመቱን ትምህርት አጠናቀኩኝ፡፡ የአስረኛ ክፍል ውጤቴን 3 ነጥብ 6 በማምጣት አልፌ ወደ መሰናዶ ት/ቤት ገባሁ፡፡
የመሰናዶ ትምህርቴን በሀዋሳ ታቦር መሰናዶ ት/ቤት በጥሩ ውጤት አጠናቅቄ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገባሁኝ፡፡
ንጋት፡– በልጅነትዎ ምን መሆን ነበር የሚመኙት?
ወ/ሮ ወይንሸት፡– ቴሌቪዥን ላይ ጋዜጠኞች ሲዘግቡ ስመለከት ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ለመግባት አስብ ነበር፡፡ በትምህርት ቤት በሚኒ ሚዲያና በተለያዩ ክበባት ላይ እሳተፍም ስለነበር ፍላጎቴ ጋዜጠኛ መሆን ነበር፡፡ ነገር ግን፤ አባቴ ሙያው ለሴት አይሆንም፤ ጋዜጠኛ ጦርነት ባለበት ቦታ ሁሉ ለዘገባ ስለሚገባ አደጋ ይኖረዋል፤ ከዚህም በተጨማሪ ጋዜጠኝነት በወጣትነት ዕድሜ ላይ ብቻ እንጂ ጋዜጠኛ ሆኖ መቅረት ጥሩ አይደለም ሲለኝ አመንኩት፡፡ አባቴን ስለምወደው የሚናገረውን እንደ ፈጣሪ ቃል አድርጌ ነበር የማስበውና በዚያ ምክንያት የእርሱን ምክር በመስማት ሶሾሎጂስት መሆንን መረጥኩኝ፡፡ በእሱም በጥሩ ውጤት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመርቄ የመጀመሪያ ዲግዬን ያዝኩ፡፡
ንጋት፡– ወደዚህ አመራርነት ከመምጣትዎ በፊት የት እና በምን ሙያ አገለገሉ?
ወ/ሮ ወይንሸት፡– በኢፌድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተቀጥሬ በከተማ ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ባለሙያ ሁኜ አገልግያለሁ፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ላለኝ ነገርም ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ሙያ ለሁለት ዓመት አገለገልኩኝ፣ ከዚያም ወደ ቀድሞ ደቡብ ክልል ጤና ቢሮ በትዳር ምክንያት ተዛውሬ ለስድስት ዓመታት በበሽታ መከላከል የሥራ ክፍል የዚህች ዩኒት መሪ እና ባለሙያ በመሆን አገለገልኩኝ፡፡ ከዚያ ደግሞ ተቋሙን ለቅቄ አማካሪ ድርጅት ከጓደኞቼ ጋር መስርተን ለሁለት ዓመታት ያህል ሰራን፡፡ በነገራችን ላይ ስራን ስትሰራ ለገንዘብ ብቻ ብለህ መስራት የለብህም፡፡ ስራ በሰራህ ቁጥር ልምዶችን በማካበት መስራትም እንዳለ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም መማር እንዳለብኝ ወስኜ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መደበኛ ፕሮግራም ተመዘገብኩኝ፡፡ ይህን የማደርገው በትዳር ውስጥ የአራት ልጆች እናት ሆኜ ነው፡፡ 2ኛ ዲግሪዬን ደስ እያለኝ ተምሬ ከዲፓርትመንቱ ሁለተኛ በመሆን በከፍተኛ ውጤት ተመረቅሁ፡፡
በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የልማት ተራድኦ ድርጅት የደቡብ ማዕከላዊ ሲኖዶስ ቅርንጫፍ ላይ በዳሬክተርነት አገልግያለሁ፡፡ ቅርንጫፉ ሲዳማን ብቻ ሳይሆን ኦሮሚያንም የሚያቅፍ ነው፡፡ እዚያም ለሁለት ዓመት ቆየሁ፡፡ በቆየሁባቸው ሁለት ዓመታት ውጤታማ ስራ ሰርቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ለተቋሙ በርካታ ፕሮጀክቶች መጡ፡፡ ብዙ አጋር አካላት አገኘ፡፡ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት በጤና፣ በውሃ፣ በማህበራዊ ጉዳይ እና በምገባ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ነገሮች ከመንግስት ጋር ብዙ ግንኙነት እንዲኖረን አድርጎናል፡፡ በዚህ መልኩ በተፈጠረው ቅርበት ይመስለኛል ክቡር ፕሬዝዳንቱ ለዚህ ቦታ ያጩኝ፡፡
ንጋት፡– አሁን በክልሉ ከፍተኛ የሀላፊነት ቦታ ላይ እያገለገሉ ይገኛሉና ወደዚህ ሀላፊነት ከመምጣትዎ በፊት ስለልማት ማህበሩ የነበርዎ ግንዛቤ እንዴት ነበር? ስለልማት ማህበሩ ዓላማ እና አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ እስኪ ያጫውቱን?
ወ/ሮ ወይንሸት፡– ወደዚህ ሀላፊነት ለመምጣት ከቤተሰብ ጀምሮ አንድ እንኳን የሚደግፈኝ ሰው አልነበረም፡፡ እኔ ግን በእንደዚህ አይነት ተቋማት ያለውን እድል ስለማውቅ ልቤ በጣም ተነሳሳ፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ከምመራው ተቋም በብዙ እጥፍ የተሻለ እድል ስለሚፈጥር፡፡ የቀደመው ቢበዛ አጋር አካላት ይኖሩት ይሆናል፡፡ ከእነሱ ጋር ተጻጽፈን ነው የምንሰራው፡፡ እዚህ ግን ህዝብ አለ፣ መንግስት አለ፣ ገቢ ማመንጫ እንዲሁም አጋር አካላት ይኖሩታል፡፡ ስለዚህ እጥፍ ድርብ እድል እንዳለው ስላወኩኝ ነበር ወደ ሲዳማ ልማት ማህበር ኃላፊነት የመጣሁት፡፡
የልማት ማህበራት ሲባል በህዝብ የሚቋቋሙ ናቸው፡፡ ማለትም መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ናቸው፡፡ ጽንሰ ሀሳቡም ዓለማቀፋዊ ነው፡፡ ለምሳሌ ወርልድ ባንክ፣ አይ ኤም ኤፍ፣ ሲዳ እየተባሉ የሚጠሩ ተቋማት ሁሉ ማህበራት ናቸው፡፡ ከፖለቲካ፣ ከሀይማኖት፣ ከዘር እና ከወገንተኝነት ነጻ የሆኑ ናቸው፡፡ ሁሉም የሚሳተፍበት መዋቅር ነው፡፡
አንዳንድ ለመንግስት የሚከለከሉ ነገሮችን ለማህበራት አዋጁ ይፈቅዳል፡፡ መንግስት መነገድ አይችልም፡፡ የልማት ማህበራት ግን መነገድ ይችላሉ፡፡ ህብረተሰቡን አሳምነው ገንዘብ መሰብሰብ ይችላሉ፡፡ ከልማት አጋሮች ጋር የፕሮጀክት ሀሳብ አዘጋጅተው ሀሳባቸው ገዢ ከሆነ ሀብት ማምጣት ይችላሉ። በመሆኑም እነዚህ ተቋማት ዓላማቸው በዋናነት መንግስት እየሰራ መድረስና መሸፈን ያልቻላቸውን ክፍተቶች እየሞሉ ህዝቡን ማገልገል ነው፡፡
በዚህ ረገድ የልማት ማህበራት በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተቋማት ናቸው፡፡ የእኛም ማህበር ከዚህ በፊት በርካታ ባለሙያዎችን ወደ ውጪ ሀገር በመላክና በማስተማር ብዙ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በሲዳማ አካባቢ ትላልቅ ቦታ የደረሱ ግለሰቦች የዚህ ማህበር አሻራ አርፎባቸዋል፡፡ እንደእነዚህ ዓይነት ነገሮችን በመንግስት ይሠሩ ቢባል የተለያዩ ትችቶች ይቀርቡበታል፡፡ ምክንቱም የመንግስትን በጀት ለምትፈልገው ሰው እንዳደረክ ተደርጎ ስለሚታሰብ እና ከአሰራርም አንጻር አግባብ ስለማይሆን የማህበራት አስተዋጽኦ እንዲህ በቀላል የሚገለጽ አይደለም፡፡
እኔም ወደዚህ ተቋም ስመጣ በርካታ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡ ቀደም ሲል ምክራቸውን አልቀበልም ያልኳቸው ሰዎች ስራውን አትወጣውም የሚል ግምት ስለሚይዙ እልህም ነበረብኝ፡፡ እኔም በባህሪዬ ያሰብኩትን ሳላሳካ እንቅልፍ የሚወስደኝ ሰው አይደለሁምና ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወደ ስድሳ ገጽ ከሰው አንጻር፣ ከፖሊሲ አንጻር ያሉ ችግሮችን ፈትሼ አወጣሁ። ከባህላዊ አሰራር ወደ ዲጅታል መቀየር እንዳለበት ለፕሬዚዳንት ጽ/ቤት አቀረብኩ፡፡
ጠቅላላ ጉባኤ እንደገና እንዲቋቋም ተደርጎ የአሰራር ስርዓቶችንና የፖሊሲ ምላሽ ማግኘት በሚችል መልኩ የማህበሩ ሪፎርም ተሰርቶ ነው ወደ ስራ የገባነው፡፡
ንጋት፡– እርስዎ ወደዚህ የልማት ማህበር ሃላፊነት ከመጡ በኋላ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትና የተመዘገቡ ለውጦች እንዴት ይገለጻሉ? በተለይ ባህላዊ የመዝናኛ ስራዎችን፥ ለምሳሌ አሞራ ገደል መናፈሻን ወይም ጉዱማሌ ፖርክ እንዲሁም የጊዳቦ ፍል ውሃን ከማልማትና ለቱሪዝም ከማስተዋወቅ አኳያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ቢያብራሩልን?
ወይዘሮ ወይንሸት፡– እኛ አሁን ላይ ጥናት አድርገን በሀዋሳ ከተማ እና ዙሪያው ባሉ ትምህርት ቤቶች የት/ቤት ምገባ ያስፈልጋቸዋል ብለን እየሰራን ነው፡፡ ሀብት ፈልገን ነው የምናመጣው፡፡ መዋቅሩ ይህን ይፈቅድልናል፡፡ ስራችንን ስንሰራ ጤና፥ ትምህርት ወይም ይህንንና ያንን ተብሎ የተገደበ አይደለም፡፡ በማንኛውም ማህበረሰብ ፍላጎት ላይ ባልተገደበ መልኩ ነው የሚሰራው፡፡ አደጋዎችም ካሉ ፈጥኖ በመድረስ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ በማድረግ ህዝባችንን እናገለግላለን። የገቢ ማመንጫዎቻችንን ለማሳደግ ጊዳቦ ላይ ጥናት አድርገን ሁለት ነገር አገኘን፡፡ አንደኛው በትንሽ ጥገና ገቢ የሚጨምሩ እንዲሁም አቅሙን በደንብ አልተጠቀምንምና ሀያ አራት ክፍል ያላቸው አራት የጋራ ባኞ ቤቶችን ጨምሮ እድሳት እንዲያገኙ ተደርጎ ገቢያችንን ወደ መቶ አራት በመቶ አሳድገን የደንበኛ እርካታና የግቢውን ውበት ቀየርን፡፡
ጉዱማሌ ላይም ጥናት አድርገን በፍጥነት መስተካከል ያለባቸውን ጉድለቶች ስንፈትሽ የአያያዝ ችግሮች መኖራቸውን አረጋገጥን፡፡ የቦታው ተፈጥሮ በጣም ቆንጆ ሆኖ ሳለ፥ ሰው ግን ለተለያዩ አላስፈላጊ ነገሮች ይጠቀምበት ስለነበር ያንን አስቆምን፡፡ ከዚያም ዙሪያ ገባውን ከፋፍተንና ባህላዊ ነገሮችን አሟልተን ካፍቴሪያ ከፈትን፡፡ የህጻናት መጫወቻ ቦታዎችንም በማመቻቸት ለጎብኚዎች ሳቢ ለማድረግ ተሞክሮ አሁን ላይ የደንበኞቻችንን ክብር በጠበቀ መልኩ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ የማህበሩ ሪፎርም የተሰራው በቅርቡ ስለሆነ ስራችንን ጨርሰናል ማለት አይደለም፡፡ በቀጣይ በርካታ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ይጠብቁናል፡፡ ወደፊት ግን ስራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ከአጋር አካላት ጋር ፕሮጀክት በመጻጻፍና ማግኘት ያስፈልጋል ብለን ስላመንን ከአራትና አምስት ወራት በኋላ ስንሞክር ወደ ሶስት ፕሮጀክቶች ነው ያሸነፍነው፣ አንዱን ከ“US AID” ጋር “GSI” ሚሊንዳ ፋዉንዴሽን እና “ILO” /ኢንተርናሽናል ሌበር ኦርጋናይዜሽን/ ጋር ትልቅ ፕሮጀክት አሸንፈናል፡፡ እነዚህ እስከአሁን የተሳኩ ሲሆን በሂደት ላይ ያሉ ሌሎችም አሉ፡፡
እነዚህ ሥራዎች ታዲያ ለማህበረሰቡ አንዳንድ ነገር ለማድረግ ጠቅመውናል፡፡ የዶሮ ፕሮጀክቶች፣ የምገባ ፕሮግራምንና ሌሎች ነገሮችን እንደ ማህበር ለህብረተሰቡ እንድንሰራ አግዞናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ጠንክረን ቀን ከሌሊት እየሰራን ማህበሩን ዳግም ተወለደ ወደሚባል ደረጃ እያመጣነው እንገኛለን። በርካታ አጋር አካላት አሁን ላይ ከእኛ ጋር ውይይት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ምናልባት በዝቶብን ካልተውነው በቀር ከእኛ የሚሸሽ ፕሮጀክት ወደማይኖርበት ደረጃ ደርሰናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ንጋት፡– በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አካባቢዎችን በማልማት፣ በትምህርት፣ በጤና እና በመልካም ስነምግባር የታነጸ ትውልድን በመፍጠር ረገድ የማህበሩ ሚና ምን ይመስላል?
ወ/ሮ ወይንሸት፡– እውነት ለመናገር የልማት ማህበሩ ሪፎርም የተሰራው በቅርቡ ነው፡፡ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ አልገባም፡፡ ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ነገሮችን እያሳየን እንገኛለን። ለምሳሌ አንድ ትምህርት ቤት በሻፋሞ ወረዳ ላይ ገንብተን ለህዝቡ አስረክበናል፣ እናቶችን ለማብቃትና ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማሳደግ የጀማመርናቸው ስራዎች አሉ፡፡ ሃምሳ እናቶችን በአምስት ቡድን አደራጅተን በዶሮ እርባታ በቂ ስልጠና ሰጥተን ለፕሮጀክቱ ደግሞ ከመድሀኒት ጀምሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን አሟልተን በሃዌላ ወረዳ እና ቱላ ላይ እየሰራን እንገኛለን፡፡ የልማት ማህበሩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ የህብረተሰቡን የማደግና የመልማት ፍላጎት በወሳኝ መልኩ ለማሟላት የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን፤ እያደረግንም እንገኛለን፡፡ እስከ አሁንም ወደ ሃያ ሺህ አባላት ናቸው በማህበሩ የሚገኙት። የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እና የአባላትን ቁጥር ለማብዛት የንቅናቄ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ንጋት፡– ለነበረን ቆይታ በድጋሚ እናመሰግናለን፡፡
ወ/ሮ ወይንሸት፡– እኔም አመሰግናለሁ
More Stories
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ግንቦት 10/2017 ዓ.ም #ደሬቴድ – ቀጥታ ስርጭት
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ግንቦት 08/2017 ዓ.ም
የቀን 6፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ግንቦት 08/2017 ዓ.ም #ደሬቴድ – ቀጥታ ስርጭት