የትምህርት ስርዓቱን የሚጎዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመስበር ትውልድን የመቅረፅ ስራ በአግባቡ መፈፀም ይገባል – የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ
የትምህርት ስርዓቱን የሚጎዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመስበር ትውልድን የመቅረፅ ስራ በአግባቡ መፈፀም ይገባል ሲሉ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ ገለጹ፡፡
”መፍጠር፣ መፍጠንና መዝለል ለትምህርት ጥራት” በሚል መሪ ቃል የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ 31ኛውን የትምህርት ጉባዔ እያካሄደ ይገኛል።
የጋሞ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አዲሱ አዳሙ (ዶ/ር)፤ በዞኑ በመፍጠር፣ በመፍጠን እና በመዝለል መርህ ዉጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንና በትምህርት ለትውልድ ኢኒሼቲቮች ህብረተሰቡን በማስተባበር ከ440 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት መሰብሰብ መቻሉን አብራርተዋል።
ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ስራው ምቹና ሳቢ የማድረግ፣ ደረጃ የማሻሻልና የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን የመሙላት ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አዲሱ አዳሙ (ዶ/ር)፤ ከተባባሪ ተቋማት ጋር በመተባበር የትምህርት ቤቶችን አደረጃጀት እና አቅም የማሳደግ ስራዎች ተሰርተዋል።
በዞኑ የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊትን ከማረጋገጥ አኳያ የተሻለ ለውጥ የመጣ ቢሆንም ከብሄራዊ ፈተና መጠነ ማለፍ አንፃር ክፍተቶች የተስተዋሉበት በመሆኑ ለቀጣይ ለስኬታማነት የባለድርሻ አካላት ርብርብ በእጅጉ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡
የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ ኢኒሼቲቭ ከቅደመ- መደበኛ እና ሁለተኛ ደረጃዎች በተቀናጀ ትብብር በርካታ መጽሀፍት በማሳተምና ለትምህርት ቤቶች በማሰራጨት የመጽሀፍ ተማሪ ጥምርታ 1ለ1 ማድረስ መቻሉ ተመላክቷል፡፡
የ7ኛ እና 8ኛ ክፍሎች ላይ ሰፊ የመጽሀፍት እጥረት መኖሩ አሳሳቢ ነዉ ያሉት የመምሪያው ኃላፊ ችግሩን ለመቅረፍ ባለድርሻዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው፤ በመፍጠር፣ መፍጠንና በመዝለል መርህ የዞኑን የትምህርት ጥራት በማረጋገጥ ለሀገር ግንባታና ለሁለንተናዊ ለውጥ መስራት ግድ ይላል ብለዋል።
በተለይም የተወዘፉ ችግሮችን በፍጥነት በመፍታት ትውልድን የመቅረፅ ሀላፊነታችንን በአግባቡ በመወጣት የትምህርት ጥራት፣ ግብዓትና ጥመርታን ማረጋገጥ ካልቻልን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አንችልም ሲሉ አሳስበዋል።
የትምህርት ስርዓቱን የሚጎዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመስበር ትውልድን የመቅረፅ ስራን በአግባቡ መፈፀም ይጠበቅብናል ያሉት አቶ ገዛኸኝ፤ ወቅቱ የሚጠይቀን አሰራሮች ላይ ትኩረት በማድረግ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ርብርብ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል።
በጉባኤውም የ2018 የትምህርት ዘመን አፈፃፀምና የ2019 ዕቅድ እየቀረበ ሲሆን በቀረበው ሪፖርትና ዕቅድ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ይደረጋል።
ለትምህርት ባለድርሻ አካላትና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ አካላት እውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
በመርሀ-ግብሩ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፣ የዞኑ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ደረጀ ጳውሎስ፣ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አዲሱ አዳሙን (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 5 ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ
የኢትዮጵያ መነሣት ኢትዮጵያዊ ተፅዕኖን ብቻ የሚያጎላ ሳይሆን አፍሪካዊ ጥንካሬም የሚኖረው ነው፡፡ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የጤና ሥርዓቷን ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየሰራች ነው ሲሉ የጤና ሚኒስትር መቅደስ ዳባ(ዶ/ር) ተናገሩ።