በንግዱ ዘርፍ ያሉ አቅሞችን በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ

በንግዱ ዘርፍ ያሉ አቅሞችን በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ

መምሪያው የ2019 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የቀጣይ 100 ቀናት እቅድ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ተመስገን እንዳሉት፤ በበጀት አመቱ ጥራት ያለው እቅድ በማቀድ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመው፤ እቅዱን በተገቢው በመተግበር የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

መምሪያው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ መኩሪያ፤ በንግዱ ዘርፍ ያሉ አቅሞችን በመጠቀም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት መሰጠቱንም ተናግረዋል፡፡

የሰንበት ገበያን በማጠናከር የተለያዩ ምርቶችን በስፋት በማቅረብ እና ህገ ወጥነትን በመከላከል ረገድ በሩብ አመቱ የተሻለ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይ አምራቹን በቀጥታ ከሸማቹ ጋር የማገናኘቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሩብ ዓመቱ ነጋዴዎች ፈቃዳቸውን እንዲያድሱና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የተከናወኑ የዲጂታል ስራዎች ውጤታማ እንደነበሩ አስረድተዋል።

በዞኑ ከ9 ሺህ በላይ የንግድ ድርጅቶች የንግድ ፈቃድ ጉድለት እንደታየባቸው አስታውሰው፤ በተሰራው ህግ የማስከበር ተግባር በቅጣት 4 ሚሊየን ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉን አብራርተዋል።

በጉራጌ ዞን ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሄሪያ ወርቁ በበኩላቸው፤ በየደረጃው የተፈጠሩ የንቅናቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት አጠናክሮ በማስቀጠል የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የ2019 በጀት ዓመት የ1ኛ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የኑሮ ውድነት እያደረሰ ካለው ጫና ማህበረሰቡን ለመታደግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አንስተዋል።

በተለይም የማህበረሰቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ፈታኝ እያደረገ ያለው የነዳጅ እጥረት ትኩረት የሚሻ ተግባር እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀጣይ በሩብ ዓመቱ በጉድለትነት የተለዩ ዘርፎች ላይ አትኩረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ምትኬ ገ/ወልድ – ከወልቂጤ ጣቢያችን