የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ እና የሌስተር ሲቲ ኮከብ ሪያድ ማህሬዝ አዲስ ክለብ አግኝቷል።

ሪያድ ማህሬዝ ለኳታሩ አል-ሻማል ፈረመ


የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ እና የሌስተር ሲቲ ኮከብ ሪያድ ማህሬዝ አዲስ ክለብ አግኝቷል።

የ35 ዓመቱ አልጄሪያዊ ተጫዋች ሪያድ ማህሬዝ ከሳውዲ አረቢያው ክለብ አል-አህሊ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ፣ አዲሱ መዳረሻው የኳታሩ አል-ሻማል ክለብ መሆኑ ተረጋግጧል።

የአፍሪካ ዋንጫ እና የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ የሆነው ሪያድ ማህሬዝ በነፃ ዝውውር የኳታር ስታርስ ሊጉን ክለብ ተቀላቅሏል።

በአሁኑ ወቅት በሊጉ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አል-ሻማል ክለብ አዲሱን ፈራሚውን በይፋ አስተዋውቋል።

ክለቡ በማህበራዊ ትስስር ገጾቹ ባስተላለፈው መልእክት“ዓለም ስሙን ያውቃል። አሁን ደግሞ የእኛን ስም ይዟል። ሪያድ ማህሬዝ እንኳን ደህና መጣህ!” በማለት ገልጿል።

ሪያድ ማህሬዝ ወደ አል-ሻማል ሲያመራ፣ በኳታር ቆይታው ከሀገሩ ልጅ እና የብሔራዊ ቡድን አጋሩ ባግዳድ ቡንጄህ ጋር እንደገና በአንድ ክለብ ውስጥ ይሠለፋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከቀድሞው የፈረንሳይ ሌንስ ተጫዋች ዌስሊ ሳኢድ እና ከቀድሞው የአርሰናል ተከላካይ ፓብሎ ማሪ ጋር በመሆን ለክለቡ ስኬት ይታገላሉ።

ማህሬዝ በፈረንጆቹ 2019 ከአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአፍሪካ ዋንጫን ያነሳ ሲሆን፣ በፈረንጆቹ 2023 ደግሞ ከእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ሲቲ ጋር የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳቱ ይታወሳል።

የኳታር ክለብ አል-ሻማል ይህንን ልምድ ያለው ተጫዋች በማስፈረሙ የቡድኑን አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠናክረው ተስፋ አድርጓል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ