ፈጣን፣ ወቅታዊና ተአማኒ መረጃዎችን ለሕብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሳውላ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገለጸ
ጽሕፈት ቤቱ የሥራ አቅሙንና የመረጃ ተደራሽነቱን ለማሳደግ ከ94 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ዘመናዊ የስቱዲዮ፣ የቢሮና የስብሰባ አዳራሽ የያዘ ሕንፃ እያስገነባ መሆኑን አስታውቋል።
በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥር የሚገኘው ሳውላ ኤፍ ኤም 102.2 ሬዲዮ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም መደበኛ ሥርጭቱን ከጀመረ ወዲህ በጎፋ፣ በባስኬቶና በኦይዳ ቋንቋዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝቡ ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።
በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሳውላ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ጌታቸው እንደገለጹት፤ ድርጅቱ አሠራሩን ለማዘመንና የመረጃ ተደራሽነቱን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል።
ከ94 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው ዘመናዊ ሕንፃ የቅርንጫፍ ጣቢያው ማኔጅመንት አካላት ምልከታ ባደረጉበት ወቅት ስራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ህንጻው
ዘመናዊ ስቱዲዮ፣ ቢሮዎች፣ የስብሰባ አዳራሽና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያካትት መሆኑን ጠቅሰው፤ የጽሕፈት ቤቱን የሥራ አቅም ለማጠናከር የሚያስችል ነው ብለዋል።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅና የይዘት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እስራኤል አመኑ በበኩላቸው፤ ጣቢያው በሦስቱ የብሔረሰብ ቋንቋዎች የሕዝቡን ባህል፣ ታሪክና የተፈጥሮ ሀብቶች በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ቅርንጫፍ ጣቢያው በአማርኛ የሚዘጋጁ ዜናዎችንና ፕሮግራሞችን ሃዋሳ ለሚገኘው የድርጅቱ ዋና ጣቢያ በመላክ የአካባቢውን የልማት እንቅስቃሴ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለሕዝቡ እንዲደርሱ እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
እየተገነባ ያለው ሕንፃም ጥራት ያላቸውን፣ ፈጣንና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑን አስረድተዋል።
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳሁን አናጋው በበኩላቸው፤ ለግንባታው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በበቂ ሁኔታ በመቅረባቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ግንባታውን በውሉ ከተያዘው ጊዜ ቀድሞ ለማጠናቀቅ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በ248 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 3 የሕክምና አገልግሎት ማዕከላት በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ተመረቁ
የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በጥራትና በፍጥነት መመለስ ለነገ የማይባል ከአመራሩ የሚጠበቅ ስራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለፁ
አካል ጉዳት ላለባቸው ህፃናት የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት አስታወቀ