የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በጥራትና በፍጥነት መመለስ  ለነገ የማይባል ከአመራሩ የሚጠበቅ ስራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለፁ

የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በጥራትና በፍጥነት መመለስ  ለነገ የማይባል ከአመራሩ የሚጠበቅ ስራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለፁ



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሀዝቦች ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች “ማንሰራራት ለክልላችን ከፍታ” በሚል መሪ ቃል ውይይት እየተደረገ ነው።



የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ የተመሰረተው የመደመር መንግስት በምርጫ ወቅት ለህዝቡ የገባውን ቃል ለመተግበር በፍጥነት ወደ ተግባር መግባቱን ጠቅሰው፤ ይህው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።



ሕዝብ የሚያነሳውን የልማትና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ መመለስ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቁመው፤ በምርጫ ቅቡልነት የገለፀውን ህዝብ በማስተባበርም የክልሉን ፀጋ አውጥቶ መጠቀም ትኩረት የሚሻ ስለመሆኑ ርዕሰ መስተዳድሩ አንስተዋል።



ዛሬ ያለው ትውልድ ካለፈው ጊዜና ትውልድ የሰፋ ፍላጎት ያለው በመሆኑ ይህንን ታሳቢ ያደረገ የመፈፀም አቅም እንደሚጠይቅ የገለፁት አቶ ፍቅሬ፤ ሁሉም አመራር በአግባቡና በሚዛናዊነት በማገልገል የህዝቡን አመኔታ ማትረፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።   

 
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ሰፊ ሀብት ያለበት መሆኑን አንስተው፤ ሀብቱን ማውጣትና መጠቀም ከተቻለ የክልሉን ህዝብ ማበልፀግ የሚከብድ አይሆንም ብለዋል።


የመደመር መንግስት ዋና መዳረሻው ሁሉን አቀፍ ብልፅግናን ማረጋገጥ በመሆኑ ለዚህ ስኬት ትጋት እና የአመራሩ ቁርጠኝነት አስፈላጊ ነው ብለዋል።


ዘላቂ የሆነ የአሰራር ስርዓት በመትከል የመደመር መንግስት የተቋም የበላይነትን ማምጣት አስፈላጊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤  የተቋም ግንባታዎችን በአግባቡ ማጠናከር ብልፅግናን ለማረጋገጥ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።


ዘጋቢ፡ ተመስገን አሰፋ – ከቦንጋ ማስተባበሪያ