አካል ጉዳት ላለባቸው ህፃናት የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት አስታወቀ።
በወልቂጤ ከተማ አካል ጉዳት ላለባቸው 258 ህፃናት በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑም ተገልጿል።
ድርጅቱ በትምህርትና በህክምና እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ ተስፋን እንደሰጣቸው ድጋፍ የተደረገላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።
የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት የፕሮጀክትና ፕሮግራም ክፍል ኃላፊ አቶ በቀለ መንግስቱ እንደገለጹት፤ የህፃናት የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ እንደመሆናቸው ከፊንላንድ ኢምባሲ ጋር በመሆን የትምሕርትና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል።
በወልቂጤ ከተማ አካል ጉዳት ላለባቸው ህፃናት እንደ ጉዳታቸው አይነት የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ በአጠቃላይ 258 ህፃናት በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምና እንደሚያገኙና በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕርሄንሲቭ ስፒሻላይዝድ ሆስፒታል ለ85 ህፃናት ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የአካል ድጋፍ ለሚፈልጉ ህፃናት እንደየጉዳታቸው አይነት የአካል ድጋፍ እንደሚሰጥ የገለጹት አቶ በቀለ፤ ሕብረተሰቡ ሕፃናትን ወደ ህክምና በመውሰድና በመደገፍ የወደፊት ሕይወታቸውን ማሻሻል አለበት ብለዋል።
በማህበረሰብ ተሀድሶ ሠራተኞችና በሕክምና ባለሙያዎች ቤትለቤት ልየታ መከናወኑን ጠቁመው፤ የቤተሰብ ግንዛቤ በማሳደግ በቤት ውስጥ ሕክምናና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከሕብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ በማድረግ መፍትሔ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሄርንሲዚቭ ስፒሻላይዝድ ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም ዶክተር አስራር ሺፋ በበኩላቸው፤ በብዛት መታከም የሚችሉና ቤተሰብ በተለያየ ምክንያት ቤት የሚያስቀሯቸው ሕጻናት መኖራቸውን ገልጸው፤ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይም ከአጥንት ጋር የተያያዙና የላንቃ ክፍተት ያለባቸው ህፃናት በጊዜ ህክምና ቢደረግላቸው ጥሩ ለውጥ እንደሚኖራቸዉ ጠቁመው፤ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ድጋፍ በመስጠት ቤት እንዳይቀሩና ለውጥ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡
የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት ህብረተሰቡ ውስጥ ገብቶ ልየታ በማድረግ ግንዘቤ ለመፍጠርና ህክምና እንዲያገኙ እያደረገ ያለው ስራው ህጻናቱ የተሻለ ሕይወት እንዲኖራቸው እንደሚያስችል ዶክተር አስራር ተናግረዋል።
አክለውም እናቶች በነፍሰጡርነት ጊዜያቸው ተገቢውን የሕክምና ክትትል ቢያደርጉ አብዛኛዎቹን ችግሮች መከላከል እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
ልጆቻቸውን ሲያሳክሙ ያገኘናቸው አቶ መልኩ አራጌና ወ/ሮ ጀሚላ ሚፍታ በሰጡት አስተያየት፤ በግንዛቤ እጥረትና በኢኮኖሚ አቅም ማነስ በልጅነት ህክምና ቦታ መውሰድ እንዳልቻሉ ገልጸው፤ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ ልማት ድርጅት በትምህርትና በህክምና እያደረገላቸው ያለው ድጋፍ ተስፋን እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ የጀመረውን ስራ ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመው፤ ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት ክትትል ማድረግና ህመም ሲኖር ህጻናትን በጊዜ ወደ ህክምና መውሰድ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡ ሄኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
በ248 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 3 የሕክምና አገልግሎት ማዕከላት በአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ተመረቁ
የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በጥራትና በፍጥነት መመለስ ለነገ የማይባል ከአመራሩ የሚጠበቅ ስራ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ገለፁ
በአካባቢያቸው በሚገኘው ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት ማግኘት እንዲቻል የተጀመሩ የጤና መሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በከምባታ ዞን የዳንቦያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ