በአካባቢያቸው በሚገኘው ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት ማግኘት እንዲቻል የተጀመሩ የጤና መሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በከምባታ ዞን የዳንቦያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ

በአካባቢያቸው በሚገኘው ሆስፒታል የተሟላ አገልግሎት ማግኘት እንዲቻል የተጀመሩ የጤና መሠረተ ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው በከምባታ ዞን የዳንቦያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ

ሆስፒታሉ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑ ተጠቁሟል።

የዳንቦያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታው ተጠናቆ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት ሳይሰጥ ለዓመታት መቆየቱን የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች ያነሳሉ።

ይሁን እንጂ በቅርቡ የተወሰኑ አገልግሎቶችን ለመስጠት የተጀመረ በመሆኑ ይህም ለአካባቢው ማህበረሰብ ልዩ ትርጉም እንዳለው ነው በሆስፒታሉ አገልግሎት ለማግኘት የተገኙና ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የሚገልፁት።

ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ሆስፒታል ባለመኖሩ የተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ ለተለያዩ እንግልቶች ሲዳረጉ እንደነበር ገልፀው አሁን የሆስፒታሉ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ቀጣይ ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመው፤ አስፈላጊው ግብዓት እንዲሟላ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አክለው ገልፀዋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አድማሱ ወዕሌቦ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ግንባታው ተጠናቆ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየው የዳንቦያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሕብረተሰቡን ብሎም መግንስታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማስተባበር ወደ አገልግሎት መግባቱን የተናገሩት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ዱባለ ናቸው።

ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት እንዳይሰጥ የግብዓት፣ የሰው ኃይልና የጤና መሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ እንዲሟሉ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የዳንቦያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የሆስፒታሉ ቦርድ ምትክል ሰብሳቢ አቶ አበበ ኤርጊቾ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አንስተው ህብረተሰቡን በማሳተፍ ግብዓት የማሟላት ሥራዎች እየተሠሩ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

አቶ አበበ አክለውም ሆስፒታሉ ቀጣይ አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶ ምቹና ዘመናዊ ሆኖ ለህብረተሰቡ ተገቢ የጤና አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ: መልካሙ ታፈሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን