የሳውላን ከተማ ገጽታ የሚቀይር የተቀናጀ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ነው – የከተማው አስተዳደር
ሳውላን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪስቶች ማራኪና ለባለሀብቶች ተመራጭ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው የተቀናጀ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እያገዘ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ገልጿል።
የሳውላ ከተማ ከንቲባ አቶ በላይነህ ባህሩ በጎፋ ዞን የምትገኘውን ሳውላ ከተማ ውብ፣ ንጹሕና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ፣ ለመዝናኛ፣ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ በተቀናጀ መልኩ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከንቲባው እንደገለጹት፣ “ሳውላን እንደገና እንሠራለን፣ ትውልድ እንገነባለን” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ውብ፣ ንጹሕና ለነዋሪዎች ምቹ በማድረግ ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ ያለመ ነው።
የልማቱ ዓላማ ከተማዋን ለመኖሪያነት ብቻ ሳይሆን፣ ለንግድ፣ ለመዝናኛና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ምቹ በማድረግ የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማጠናከር መሆኑንም አቶ በላይነህ አስረድተዋል።
ለልማቱ ውጤታማነት የሕብረተሰቡና የባለሀብቱ ንቁ ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባው፣ የተጀመረው ሥራ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ የሁሉም ወገኖች ትብብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሳውላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ጳውሎስ በበኩላቸው፣ የተጀመረው የተቀናጀ ዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታ የከተማዋን ገጽታ እየቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።
በልማቱ ውስጥ ዘመናዊ የመንገድ መብራቶች፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የመናፈሻ ሥፍራዎች፣ የሕዝብ መገልገያ ካፌዎች፣ የሕፃናት መጫወቻዎችና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች መካተታቸውንም አቶ ፍጹም አብራርተዋል።
እነዚህ የመሠረተ ልማትና የማኅበራዊ መገልገያ ሥራዎች ለከተማዋ ውበት ከሚኖራቸው አስተዋጽኦ ባሻገር፣ የነዋሪዎችን ምቾት ለማሳደግና ለማኅበራዊ ግንኙነትና መዝናኛ የተሻለ አማራጭ ለመፍጠር ያግዛሉ።
የከተማዋ ነዋሪዎችም ከተማ አስተዳደሩ ሳውላን ለነዋሪዎች ምቹ፣ ለቱሪስቶች ማራኪና ለባለሀብቶች ተመራጭ ለማድረግ እያከናወነ ያለውን ሥራ አድንቀዋል።
ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ከከተማው አስተዳደር ጎን በመቆም የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የሳውላ ከተማን ጽዱ፣ ምቹና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ማዕከል የማድረጉ ሥራ የአስተዳደሩን ጥረት ከሕብረተሰቡና ከባለሀብቱ ተሳትፎ ጋር በማጣመር ወደ ተግባር እየተቀየረ ይገኛል፡፡
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
የቡና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚያስችሉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ
የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጅ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተገለጸ
አፍሪካ የዓለም አቀፉን የኢነርጂ ሽግግር ታፋጥን ይሆን?