የቡና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚያስችሉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ

የቡና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚያስችሉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ

‎

‎በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ከጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ውስጥ ለሚገኙ አርሶ አደሮች፣ የተደራጁ ወጣቶችና ባለሀብቶች በምርምር ውጤታማነታቸው የተለዩና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ልዩ የቡና ዝርያዎችን እያቀረበ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

‎የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር ደረጀ ቱሉ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ በምርምር ካገኛቸው 14 የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ውስጥ ዘጠኙ ላይ ትኩረት በማድረግ እያሰራጨ መሆኑን ገልፀው፤ ምርታማነቱን በሄክታር ከ22 ኩንታል በላይ ማድረስ እንደተቻለም ገልጸዋል።

‎

‌‎በበጀት አመቱ ከ40 ኩንታል በላይ የቡና ምርጥ ዘር እንዲሁም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ማሰራጨቱን ጠቅሰው፤ በሞደል አርሶ አደሮችና በተደራጁ ማህበራት በኩል ማዕከሉ ድጋፍና ክትትል በማድረግ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቡና ችግኞች እያዘጋጀ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

‎

‌‎በማዕከሉ የቴክኖሎጂ ብዜትና ዘር ምርምር የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ በኃይሉ መኮንን በበኩላቸው፤ የተሻሻሉና የተለያዩ የምርመራ ደረጃዎችን ያለፉ የቡና ዝርያዎችን ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ የማድረግ ኃላፊነቱን አጠናክሮ መቀጠሉን  ገልፀው፤ የቆላና የወይና ደጋ የቡና ዝርያዎች ላይ  ትኩረት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

‎ወቅቱ የቡና ዘር ዝግጅት የሚደረግበት በመሆኑ የአርሶ አደሩንና የግል ባለሀብቶችን ፍላጎትና  የአካባቢውን ሥነ ምህዳር መነሻ ያደረገ እና በሁለት ዓመት ውስጥ ምርት መስጠት የሚችሉ የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር ሌሎች ተያያዥ የምርምር  ስራዎችንም  እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።

‎

‌‎የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ ባለሙያዎችን  ከማሰማራት ጀምሮ በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችና ለተደራጁ ማህበራት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ላይ ትኩረት መደረጉን አቶ በኃይሉ አክለዋል።

‎‎የቡና ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ   በምርምር ማዕከል በሚደረገው ጥረት ልክ  አርሶ አደሩና በዘርፉ የተሰማሩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን  ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል።

‎

‎የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል  ለበርካቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የገለጹት አስተያየት የሰጡ አንዳንዳድ ሰራተኞች በበኩላቸው፤ ከወርሃዊ ገቢያቸው ባሻገር ምርጥ የቡና ዘር ዝግጅት ላይ በሚሰጣቸው ስልጠና የተለያዩ  ሙያዎችን እየቀሰሙ መሆናቸውን አንስተዋል።

‎

‎በብሔራዊ ደረጃ ከሚገኙ 23 የግብርና ምርምር ማዕከላት አንዱ የሆነው የቴፒ ግብርና ምርምር ማዕከል በተለይ ምርታማነታቸው በምርምር የተረጋገጡና የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎች ላይ   የምርምር ተግባራትን በማጠናከር ላይ ይገኛል።

‎

‎ማዕከሉ ከቡና ባሻገር በቅመማ ቅመም፣ በእርባታ፣ በካካዎ፣ በበርን ኮምፖስት እና በሌሎች   ቴክኖሎጂ ተኮር  ዘርፎች ላይ በስፋት እየሰራ ያለ ተቋም ሲሆን አሁን ላይ ከ100 በላይ ቋሚና ከ650 በላይ  ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ከማዕከሉ የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

‎

‎ዘጋቢ: ታሪኩ ታደሰ – ከማሻ ጣቢያችን