አርሰናል ሰራተኞቹን ከስራ ሊያሰናብት ነው

አርሰናል ሰራተኞቹን ከስራ ሊያሰናብት ነው

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ አርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ ዋንጫ ባነሳበት እና በታሪኩ ከፍተኛውን የገቢ መጠን ባስመዘገበበት በዚህ ወቅት፣ 60 የስራ መደብ ሰራተኞቹን ከስራ ለማሰናበት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።

ክለቡ ይህንን መረጃ ለሰራተኞቹ ያሳወቀ ሲሆን፣ የሰራተኞች ቅነሳው በተለያዩ የስራ ክፍሎች ላይ የሚተገበር ይሆናል።

ሆኖም ውሳኔው ከመጽደቁ በፊት የውይይት እና የምክክር ሂደቶች እየተካሄዱ በመሆናቸው ሊሻሻል ወይም ሊለወጥ እንደሚችል ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።

ምንም እንኳን የሰራተኞች ቅነሳው በርካታ ዘርፎችን የሚያካትት ቢሆንም፣ የወንዶች እና የሴቶች ቡድን አሰልጣኞች እንዲሁም የክለቡ ስፖርታዊ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖች፣ የታዳጊዎች አካዳሚ፣ የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ እና የአርሰናል ፋውንዴሽን፣ የጸጥታና ደህንነት ሰራተኞች እንዲሁም ለሴቶች ቡድን የተመደቡ ልዩ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ክፍሎች ግን ከተያዘው አቅድ ውጭ እንደሆኑ ታውቋል።

ይህ የሰራተኞች ቅነሳ እቅድ ይፋ የሆነው ክለቡ ስኬታማ የውድድር ዘመን ባሳለፈበት ማግስት መሆኑ በርካቶችን አስገርሟል።

አርሰናል ባለፈው የ2024-25 በጀት ዓመት የ691 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን እና የነበረበትን አጠቃላይ ኪሳራ ወደ 1.4 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ዝቅ በማድረግ ሙሉ በሙሉ አትራፊ ለመሆን እንደተቃረበ ማስታወቁ ይታወሳል።

በተለይም የንግድ እና የስፖንሰርሺፕ ገቢው ከ218.3 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ 263.2 ሚሊዮን ፓውንድ ያደገ ሲሆን፣ ለዚህም ከሶባ ሪያሊቲ ጋር የተደረገው የመለማመጃ ሜዳ የስያሜ ባለቤትነት ስምምነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተገልጿል።

ውሳኔው ይፋ የሆነው የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ እስከ 2030 የሚያቆያቸውን አዲስ ውል በተፈራረሙ በሳምንቱ ነው። ይህ አዲስ ውል አርቴታን በፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኙ አሰልጣኝ እንዳደረጋቸው ይነገራል።

አርሰናል እ.ኤ.አ በነሐሴ 2020 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት 55 ሰራተኞችን ከስራ ማሰናበቱ ይታወሳል።

በወቅቱ ተጫዋቾች የደሞዝ ቅነሳ አድርገው እያለ የተወሰደው የሰራተኞች ቅነሳ እርምጃ በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ የነበረ ሲሆን፣ አሰልጣኝ አርቴታ የክለቡን እርምጃ ተከላክለው እንደነበር አይዘነጋም።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ